የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር “አራት ግቦች” እንዳሉት አሜሪካ ገለጸች

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የህወሓት የሰላም ንግግር መራዘም፤ ሁለቱ ወገኖች “የተራራቀ” አቋም ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን እንደሚጠቁም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የሰላም ንግግር የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት “ልዩነታቸውን የሚወያዩበት እና በመካከላቸው ያለውን ርቀት ማጥበብ የሚቀጥሉበት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ቃል አቃባዩ ይህን ያሉት፤ ስምንተኛ ቀኑን ስላስቆጠረው የኢትዮጵያ መንግስት እና የህወሓት የሰላም ንግግርን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ትላንት ምሽት በሰጡት መግለጫ ነው።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተጀመረው የሰላም ንግግር እስከ እሁድ ጥቅምት 20 እንደሚቆይ የደቡብ አፍሪካ መንግስት አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ ንግግሩ እስከ ትላንት ምሽት መቀጠሉን ከቦታው የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።

በፕሪቶሪያ ከተማ እየተካሄደ ለሚገኘው ለዚህ የሰላም ንግግር የተቀመጠ የቀን ገደብ እንደሌለ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ቃል አቃባይ ኤባ ካላንዶ ትላንት ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

በንግግሩ ላይ በ“ተሳታፊነት እና በታዛቢነት” እየተካፈሉ የሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር፤ ንግግሩ እስከሚያበቃበት ዕለት ድረስ በደቡብ አፍሪካ እንደሚቆዩ ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል።

እንደ ኢትዮጵያን ኢንሳይደር ዘገባ የሰላም ንግግሩ እስከ ረቡዕ ድረስ ይቀጥላል መባሉ የሂደቱን አለመሳካት ያመልክት እንደሆነ የተጠየቁት ፕራይስ፤ ሁለቱ ወገኖች “የተራራቀ” አቋም ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን የሚጠቁም ነው ብለዋል።

የሰላም ንግግሩ መራዘም ሁለቱ ወገኖች “አብረው ለመቀመጥ ፈቃደኛ ሆነው መቀጠላቸውንም አመላካች” ጭምር ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

የደቡብ አፍሪካው ውይይት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት “ልዩነታቸውን የሚወያዩበት እና በመካከላቸው ያለውን ርቀት ማጥበብ የሚቀጥሉበት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ሀገራቸው ከሰላም ንግግሩ የምትጠብቀውን አመልክተዋል።

ፕራይስ በትላንቱ ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር አራት ግቦች እንዳሉት አስረድተዋል።

አፋጣኝ የግጭት ማቆም ላይ መድረስ፣ ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ እና የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ መውጣታቸውን ማረጋገጥ ፕራይስ የጠቀሷቸው የሰላም ንግግሩ አራት ዋነኛ ዓላማዎች ናቸው።

በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ የሚገኘው የሰላም ንግግር ሁለቱ ወገኖች ”ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ” እና ለአራቱ ግቦች ስኬት “መልካም ዕድል” እንደሆነ ቃል አቃባዩ ጠቅሰዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.