የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የመክሰስ ፍላጎት የለኝም አለ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የህግ ፣ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የ2015 በጀት ዓመት እቅድ እና የ2015 የመጀመሪያዉ ሩብ አመት አፈጻጸም ላይ ትናንት ዉይይት አድርጓል፡፡

በዉይይቱ ላይ የተገኙት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ብርሀነመስቀል ዋቅጋሪ እንደገለጹት፣ ዘመናዊ ህንጻ ለመስራት አቅደዉ የከተማ መስተዳድሩ ካርታዉን በማምከኑ ምክንያት የጨረታ ሰነድ ለማዉጣት አለመቻላቸዉን ተናግረዋል፡፡

አሁን ያለዉ ህንጻ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ሀገራችን ካላት የህዝብ ቁጥር እና ከምታስተናግዳቸዉ ጉዳዮች አንጻር የማይመጣጠን ስለሆነ አዲስ ህንጻ መገንባት ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡

‹‹ቦታዉን አጥረን ዲዛይን ጨርሰን ብንቀመጥም፣ ካርታዉ በመምከኑ እና ሊዝ በመቋረጡ ምክንያት የጨረታ ሰነዱን አየር ላይ ማዉጣት አልቻልንም ››ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሚሰበስቡት ሁነት ላይ የተወሰኑ መፍትሄዎችን ለማበጀት ተሞክሯል ያሉት አቶ ብርሀነመስቀል ዋቅጋሪ፣ ምክርቤቱ እንዲያግዘን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

‹‹የፌደራል መንግስት በጀት እስከመደበለት ድረስ የማይጀመርበት ምክንያት መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ጉዳዩ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነዉ በሚል ዉሉ ሲቋረጥ እና ካርታ የማምከን ስራዉ ሲሰራ እንደ ፌደራል ፍርድ ቤቶች ቁጭ ብለን መክረንበት ‹‹መካሰስ ጠቃሚ አይደለም›› ብለን ትተን በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር እና መግለጫ ለመስጠት ቀጠሮ ብንይዝም ከንቲባዋ ስላልተገኙ እና በሌሎች ምክንያቶች ጉዳዩ ሳይቋጭ ቀርቷል ብለዋል፡፡

‹‹ጉዳዩን የሀገር አጀንዳ አድርገን በማየታችን እንጂ የኛዉ ጠበቆች መጥተዉ ፍትህ የማግኘት መብታችን ነዉ የተነካዉ ስለዚህ እንከሳለን ቢሉም አሁን ያለዉን አማራጭ መፍትሄ እንጠቀምበት እና ቀሪዉን የምናየዉ ይሆናል ብለን ትተነዋል›› ነዉ ያሉት ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከ21 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ መሬት ላይ ለማስገንባት አቅዶ የነበረዉ ህንጻ ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ የታሰበ ነበር፡፡

በእስከዳር ግርማ
ጥቅምት 25 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.