በአዲስ አበባ ከ66ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገ ጥናት ወደ 66ሺህ 575 የሚጠጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ከኮተቤ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በተደረገ ጥናት በከተማዋ ወደ 66ሺህ 575 የሚጠጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡

የቢሮዉ ሀላፊ ዶክተር ሀና የሺንጉስ እንደገለጹት፣ እስካሁን በተደረገ ጥናት በከተማዋ ይህን ያህል ቁጥር ያለዉ የጎዳና ተዳዳሪ መኖሩን ለማወቅ ችለናል ብለዋል፡፡
ሀላፊዋ ከዚህ ቁጥር ዉስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ከ 10-40 ዓመት የዕድሜ ክልል ዉስጥ ያሉ መሆናቸዉን ገልጸዉ፣ ይህም አምራች የሚባለዉ የዕድሜ ክልል መሆኑን በማንሳት እንደ ሀገርም ብዙ እያጣን ነዉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ቁጥር መበራከት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰዉ በቤት ዉስጥ የሚደርስ ጥቃት መሆኑም የተገለጸ ሲሆን ፣ በቤተሰብ መካከል የሚፈጠር አለመግባባት እና ቤተሰብ በፍቺ መለያየት ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ናቸዉ ተብሏል፡፡

ሌላዉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣዉ በግጭት እና ጦርነት ምክንያት አከባቢያቸዉን ጥለዉ የሚሰደዱ ህጻናት ቁጥር መበራከት ሲሆን ይህም ለጎዳና ላይ ህይወት በይበልጥ የሚያጋልጣቸዉ መሆኑም ተነስቷል፡፡

በቤተሰብ እና በማህበረሰብ እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት የሚፈጸመዉ የህጻናት ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የገለጹት ዶክተር ሀና የሺንጉስ፣ ይህ ጉዳይ የሴቶች ፣ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስራ ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እንዲሁም እንደ ሀገር ሁሉም ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተዉ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዙሪያ ሌሎች እየተደረጉ ያሉ ጥናቶች መኖራቸዉን የገለጹት ሀላፊዋ፣ ሁሉም በጊዜ ሂደት ይፋ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በ10 ዓመት ጊዜ ዉስጥ ይህ ቁጥር ወደ 100ሺህ ያድጋል ተብለናል ያሉት ሀላፊዋ፣ እዛ እስኪደርስ ግን አንጠብቅም የተለያዩ ስራዎችን እንሰራለን ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ህዳር 09 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.