ከሽምብራ ዱቄት የተሰራ ብስኩት ለገበያ ሊቀርብ ነዉ፡፡

በሃገራችን ከተለመደው የብስኩት አመራረት በተለየ መልኩ የተመረተው የሽምብራ ዱቄት ብስኩት ለገበያ ሊቀርብ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከገበሬዎች በተገኘ የሽምብራ ምርት የተቀነባበረው “ሰኒ “ ብስኩት ለገበያ ብቁ መሆኑን ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ማረጋገጫ ማግኘቱን “የዲሲኤ” ግብረ ሰናይ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር አና ሃፍ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ለህጻናት እና ለነፍሰጡር እናቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለዉ የተነገረው ይህ ብስኩት፣ ከፍተኛ የሆነ የፕሮቲን ይዘት እንዳለውም ዳይርክተሯ ገልጸዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2019 በተሰራ ጥናት በኢትዮጵያ በርካታ ህጻናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች ከፕሮቲን እጥረት የተነሳ ለበሽታ እንደሚጋለጡ ያሳያል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሽንብራ እና መሰል ጥራጥሬዎች ከፍተኛ ፕሮቲን እንዳላቸዉ የገለጹት አና ሃፍ የህጻናትን እና የእናቶችን ጤንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከገበሬዎች በተገኘ የሽንብራ ምርት ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከሞያ ፉድ ኮምፕሌክስ ጋር በመተባበር ባደረገው የምርት ሙከራ “ሰኒ” ብስኩት ውጤታማ ሆኖ በሚመለከተው አካል ለገበያ ብቁ መሆኑ ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ እንደ ሞያ ፉድ ኮምፕሌክስ ሁሉ ሌሎች የግል ባላብቶችም በገበሬዎች እጅ የሚገኙ ሽምብራ፤አተር እና መሰል ጥራጥሬዎች በመጠቀም ወደ ምርቱ እንዲገቡ መክሯል፡፡

የጥራጥሬዎች እጥረት ሊከሰት ስለሚችል ፤መንግስት ወደዚህ ስራ ለሚገቡ ባላብቶችን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግም ተጠይቋል፡፡

ዲሲኤ” ግብረሰናይ ድርጅት መሰረቱን ዴንማርክ ያደረገ ተቋም ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ 45 አመታት አስቆጥሯል፡፡

ግብረ-ሰናይ ድርጅቱ በሴቶች እና ህጻናት ጤና ዙሪያ እየሰራ እንደሚገኝም ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

በመሳይ ገ/መድህን
ህዳር 09 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.