የኢትዮጵያ የስርዓተ -ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ እንደ ተቋም ባለመመዝገቡ ቅር መሰኘታቸውን ሊቀ-መንበሯ ወ/ሮ እስራኤል ሀይሉ ገለጹ፡፡

እንደ ተቋም አለመመዝገቡም ከመንግስት ሊያገኝ የሚገባዉን ድጋፍ እንዳያገኝና ብዙዎችን ተደራሽ እንዳያደርግ መሰናክል ሆኖበት መቆየቱን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የስርዓተ-ምግብ መሪዎች ኔትወርክ ከተቋቋመ አራት አመታት ቢሆኑትም እስካሁን ድረስ እንደ ተቋም ህጋዊ ሰዉነት አለማግኘቱ ተገልጿል፡፡

የኔትወርኩ መስራች እና ሊቀመንበር ወ/ሮ እስራኤል ሀይሉ እንደገለጹት፣ ይህ ኔትዎርክ በነጻ እና በበጎ ፍቃደኝነት የሚያገለግሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ስብጥር መሆኑን አንስተዉ እስካሁን ድረስ ግን ህጋዊ ሰዉነት አለማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

በነዚህ አራት አመታት ጊዜ ዉስጥ ሀገራችን የምትሰራቸዉን ስራዎች በመደገፍ የተለያዩ እገዛዎችን ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ሊቀመንበሯ ወቅታዊ የሆነ ስልጠና በመስጠት ፣ በድርቁ እና በነበረዉ የተለያዩ መፈናቀሎች የተጎዱ አባወራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

የኔትወርኩ አባል በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ የተሰማራ ነዉ ያሉት ወይዘሮ እስራኤል ፣አባላቱ በወር 8 ሰዓት ነጻ የስለጠና አገልግሎት እንዲሁም ደግሞ በድርቁ ለተጎዱት ሀብት በማሰባሰብ ሲሰሩ ነበር ብለዋል፡፡

ስልጠናዉ ሲሰጥ ሁሉም ከራሱ አልፎ ሌላዉንም፣ ሀገሩንም እንዲለዉጥ ይጠበቃል ያሉት ሊቀመንበሯ፤ አገራችን ያስቀመጠቻቸዉን ፖሊሲዎች፣ስትራቴጂዎች እና ፕሮግራሞችን ለመደገፍ ከዋናዉ ሰዓት በተጨማሪ ሽፋን በመስጠት ሁሉንም የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የስርዓተ-ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ አራተኛዉ ዓመታዊ ጉባኤም ‹‹ የስርዓተ-ምግብ አመራር ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ-ምግብ በኢትዮጵያ›› በሚል በትናንትናዉ ዕለት ተካሂዷል፡፡

ኔትወርኩ ህጋዊ ሰዉነት ኖሮት ከመንግስትም እገዛ ተደርጎለት ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ ስራ ለመስራት እያመቻቸ ዕቅዱንም ወደ ትግበራ እየቀየረ ባለበት ወቅት ጉባኤዉ መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ህዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.