በጉራጌ ዞን 41 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ፡፡

በዞኑ ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ያልተገባ እንቅስቃሴ አድርገዋል የተባሉ 41 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ክልሉ አስታውቋል፡፡

የደቡብ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች እረብሻ እና ብጥብጥ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉ 41 ያህል ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል ብለዋል፡፡

ከልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በዞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር ከሰሞኑ ዞኑ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ መደረጉ ይታወሳል፡፡

የጉራጌ ዞን በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን የተደረገው፤ ከክልል አደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር “በመደበኛ አሰራር ለማስተዳደር” ባለመቻሉ መሆኑን አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

ከዚሁ የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የጸጥታ ችግር ተፈጥሮ እንደነበረ የተናገሩት አቶ አለማየሁ በህዝቡና በመንግስት ንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ መቆጣጠር ተችሏል ሲሉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው ጸጥታን የማስከበር ስራ፤ በድርጊቱ ተሳተፈዋል የተባሉ ከ70 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ አለማየሁ ነግረውናል።

በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ገልጸው ህግ የማስከበሩ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ህዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *