ኢትዮጵያ ቻይና በሰጠችው ከታሪፍ ነፃ ዕድል ሳትካተት ቀረች፡፡

በሰነድ መዘግየት ምክንያት ኢትዮጵያ ቻይና ላላደጉ አገሮች በሰጠችው ከታሪፍ ነፃ ዕድል ሳትካተት መቅረቷ ተነግሯል፡፡

ቻይና ወደ አገሯ ምርቶችን ለሚያስገቡ ያላደጉ አገሮች እ.ኤ.አ. ከታኅሳስ 1 ቀን 2022 እንዲጠቀሙበት ባቀረበችው የታሪፍ ነፃ የገበያ ዕድል አሥር አገሮች ሲመረጡ፣ ኢትዮጵያ ተዘጋጅቶ መቅረብ የነበረበትን ሰነድ በማዘግየቷ ምክንያት ሳትካተት መቅረቷ ታውቋል፡፡

ከኤዥያ አፍጋኒታን፣ እንዲሁም ዘጠኝ የአፍሪካ አገሮች የተካተቱበት አሥሩ የተመረጡት አገሮች 98 በመቶ የሆኑ ገቢ ቀረጥ የሚጣልባቸውን ምርቶችን ወደ ቻይና ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ማስገባት እንደሚችሉ፣ የቻይና መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡

ይህም የቻይና መንግሥት፣ ‹‹የዓለም አቀፉ ምጣኔ ሀብትን ለማበረታታት›› በሚል የወሰነው ፖሊሲ፣ ሌሎች ያላደጉ አገሮችንም ሊያካትት እንደሚችል ተገልጾ ነበር፡፡

የተለያዩ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቻይና በኩል ነፃ ታሪፍ የተፈቀደላቸው ዝርዝር ምርቶችን ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በቻይና ኤምባሲ በኩል ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ ኤምባሲው ግን በአፋጣኝ መልስ አላገኘም፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ኤምባሲው በጉዳዩ ላይ አብረው እየሠሩ እንደሆነ የጠቀሱት ምንጮች፣ የሰነዱ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ፀድቆ እንደተሰጣቸውም ኢትዮጵያ ልትካተት እንደምትችል ተናግረዋል፡፡

‹‹ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሸጋገርና ኢትዮጵያን ቀጣይ ተጠቃሚ አገር ለማድረግ የሚኒስቴሩ መልስ እየተጠበቀ ነው፤›› ሲሉ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከበርካታ ወራት በፊት ቻይና ኢትዮጵያን በፖሊሲው አንደኛዋ ተጠቃሚ አገር እንደምትሆን አረጋግጣም ነበር፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ኢትዮጵያ የዚህ ነፃ ታሪፍ ተጠቃሚ እንደምትሆንና የሒደት ጉዳይ እንጂ ዕድሉ አምልጧት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ከኤምባሲውም ጋር በተደጋጋሚ እየተገናኙ እንደሚሠሩ፣ የምርቶቹን ዝርዝርም ተቀብለው ኢትዮጵያ ልትልካቸው የምትችላቸውን ዝርዝር ምርቶች ከቻይንኛ ወደ አማርኛ ለማስተርጎም እየሠሩ እንደሆነ አክለው ገልጻዋል፡፡

‹‹በቻይና የተጻፈ ሰነድ ስለሆነ ዝርዝሩን ወደ እኛ ኮድ ለማስተርጎም፣ እንዲሁም እኛ ልንልካቸው የምንችላቸውን ምርቶች ለመለየት እየሠራን ነው፡፡ ለንግዱ ማኅረበሰብም በቅርቡ አከፋፍለን እንዲሠሩበት ይደረጋል፤›› ሲሉ አቶ ሙሴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ከምትልካቸው አብዛኛዎቹ ምርቶች የግብርና ውጤቶች እንደመሆናቸውና ቻይናም የግብርና ምርቶችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከአፍሪካ ሲሄዱ በዚህ ፖሊሲ እንዲጠቀሙ መፍቀዷ የሚታወስ ነው፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ታህሳስ 03 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.