የነዳጅ ድጎማው ለሌብነት መጋለጡ ተሰማ፡፡

የነዳጅ ድጎማው ከታለመለት አላማ ውጭ ለሌብነት መጋለጡን፣ ኮንትሮባንድና ብክነትም በስፋት እየተስተዋለበት መሆኑ በጥናት ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የታለመው የነዳጅ ድጎማ አተገባበርና በአፈፃፀም ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን የዳሰሰ የጥናት ውጤት ይፋ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ
የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አተገባበር ሰፊ ክፍተቶችና ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።

በተለይ የነዳጅ ማደያዎችና ችርቻሪዎች አካባቢ ሌብነትና ህገ ወጥነት እንዲሁም የኮንትሮባንድና ብክነት በስፋት የሚስተዋል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም አልፎ ድጎማው ከህብረተሰቡ ይልቅ አሽከርካሪዎች ባልተፈለገ መልኩ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸው ድጎማ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መደበኛ አገልግሎት መስጠት ትተው በኮንትራት ስራ ላይ መሰማራታቸውንም ተናግረዋል።

የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው የ90 ብር ታሪፍ እስከ 200 ብር እንዲሁም የ300 ብር ታሪፍ እስከ 600 ብር እያስከፈሉ መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ በትራንስፖርት ስምሪት አካባቢ የተቀናጀ ስምሪትና ቁጥጥር ያለመኖር፣ የንግድና የትራንስፖርት ዘርፉን የሚመሩ የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣትና ቅንጅታዊ አሰራር ደካማ መሆን ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሰራር ማጠናከር፣ ድጎማውን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በ’ጂፒ ኤስ’ ቴክኖሎጂ መቆጣጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቅረፍ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ዓላማን መሰረት ያደረገ አሰራርና የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚገባ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አተገባበሩ ወጥና ውጤታማ እንዲሆን ከፌዴራል ጀምሮ ክልሎች፣ የከተማ መስተዳድሮች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ጨምሮ አዋጁን በባለቤትነት መፈጸም እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ታህሳስ 06 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.