ለ8 ቀናት ስልጠና የ30 ቀናት አበል የከፈለው ማዕከል ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ያለ አግባብ ወጭ አድርገሃል ተብሎ ተተቸ፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል 2.9 ሚሊየን ብር ያለ አግባብ ወጪ የተደረገ ክፍያ ማካሄዱ ተገልጿል፡፡

የቀድሞዉ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስተሪ ልማት ኢንስቲትዩት የአሁኑ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ሰፋ ያለ የስነምግባር ብልሽትና የአሰራር ክፍተት አለበት ተብሏል፡፡

የማዕከሉ የ2013 በጀት ዓመት ሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት ሪፖርት ለመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበበት ወቅት ከፍተኛ የኦዲት ግኝት መገኘቱ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በማዕከሉ የተገኘዉ ግኝት ከዚህ በፊት በዩንቨርሲቲዎች ይስተዋል የነበረ ችግር መሆኑን አንስተዉ፤ ከአበል አከፋፈል ጋር በተያያዘ ማዕከሉ ግኝት እንደተገኘበት ገልጸዋል፡፡

የምርምር ጥናቱ አዳማ ተካሂዶ ሀዋሳ ነዉ ተካሄደዉ በሚል ክፍያዎች እንደሚፈጸሙ በማስረጃ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቢሯቸዉ ተቀምጠዉ ዝግጅቱ አዳማ እንደተካሄደ በማድረግ ሰራተኞች አበል እንዲከፈላቸዉ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

ለ 8 ቀናት የተዘጋጀ ስልጠና እና ጥናት የ 30 ቀን አበል ይከፈላቸዋል ያሉት ዋና ኦዲተሯ፣ በማስረጃ ጭምር አረጋግጠናል ሲሉ ነዉ ለምክር ቤቱ አባላት የገለጹት፡፡

በተጨማሪም ከተለያዩ ሆቴሎች ጋር በመነጋገር መስክ (ፊልድ) ሳይወጡ እዛዉ ቢሯቸዉ ዉስጥ ሆነዉ ከኢቨንቱ እና ከግኝቱ ጋር ተመሳሳይነት የሌለዉ ሰነድ አቅርበዉ ከ4 መቶ ሺህ ብር በላይ አበል እንዲከፈል ማድረጋቸዉንም ገልጸዋል፡፡

‹‹ቃል በቃል ይሄ ገንዘብ ተዘርፏል ነዉ የምለዉ›› ያሉት ወይዘሮ መሰረት ገንዘቡ መመለስ አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዉ ተናግረዋል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.