አሸባሪውን የሸኔ ታጣቂ ሃይል የመደምሰስ ዘመቻ አካል በሆነውና በደቡብ ኦሮሚያና አዋሳኝ አካባቢዎች የተሰማራው ጥምር ጦር በሸኔ ይዞታ ሥር የነበሩ በርካታ ቀበሌዎችን ማስለቀቅ መቻሉን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል፡፡
የአሸባሪው የሸኔን ታጣቂ ሃይል የመደምሰስ ዘመቻ አካል በሆነውና በደቡብ ኦሮሚያና አዋሳኝ አካባቢዎች የተሰማራው ጦር በሸኔ ይዞታ ስር የነበሩ በርካታ ቀበሌዎችን ማስለቀቅ ችሏል፡፡
ዘመቻውን የሚመሩት የመከላከያ ከፍተኛ መኮንን እንዳሉት አሸባሪው የሸኔ ታጣቂ ሃይል በኦሮሚያ ክልል የሚያደርሳቸውን ህዝባዊ ጥፋቶች በመግታት የተረጋጋ ቀጠና ለመፍጠር የፀጥታ አካላት በተቀናጀ መንገድ ወደ ትግበራ ገብተዋል።
በደቡብ ኦሮሚያ በሚገኙ ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ እንዲሁም ቦረና ዞኖችን ማዕከል አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ጦር ስኬታማ ተልዕኮ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ከፍተኛ መኮንኑ ባደረጋቸው የተጠኑ ዘመቻዎችም በሸኔ ይዞታ ስር የነበሩ ሰባት ቀበሌዎች ነፃ መሆናቸዉን መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

የምስራቅ ጉጂ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሀሩ ገርማ የህዝብና የሃገር ጠላት የሆነውን የሸኔ ታጣቂ ሃይል ከቀጠናው በማጥፋት መላውን ህዝብ ወደሚፈልገው የሰላም አየር መመለስና ማህበረሰቡ ከስጋት ነፃ እንዲሆን ለማስቻል እንደ ሰራዊቱ ህዝቡም የዚህ ዘመቻ ግንባር ቀደም መሪ መሆን ይገባዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ለህዝብ ጥቅም እቆማለሁ በሚል ማጭበርበሪያ ማህበረሰቡን ለዘርፈ ብዙ ችግሮች የዳረገውን የሸኔ ታጣቂ ሃይል ከቀጠናው ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ውስጥ በየአካባቢው ያለው ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ሁሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የተጀመረው ዘመቻ በቀጠናው ስር ያለውን የሸኔ ታጣቂ ሃይል መደምሰስና የተረጋጋ ቀጠና መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆኑን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ታህሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም











