የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ኮሚሽኑ በዓሉን አስመልክቶ ከእሳትና የኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታ መጨመርና ሰፊ የመዝናናት እንቅስቃሴ አንጻር ሊከተል የሚችለዉን የእሳት ቃጠሎና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ከወዲሁ ትኩረት በመስጠት ለመከላከል እንዲቻል ከጥንቃቅ ጉድለት የሚመጡ አደጋዎችን ለማስቀረት ህብረተሰቡ የበኩሉን ጥንቃቅ እንዲያደርግ ነዉ መልዕክቱን ያስተላለፈዉ፡፡

በዚህም ህብረተሰቡ በመኖሪያ ቤትና ምግብ በሚያሰናዱ ተቋማት የጧፍ ፣ የጋዝና የኤሌክትሪክ ምድጃዎችን አግባብ ባልሆነ መንገድ ከመጠቀም እንዲቆጠብ መልዕክቱን ያስተላለፈ ሲሆን፣ የከሰል ምድጃ በቤት ዉስጥ በምጠቀምበት ጊዜ በርና መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር ማድረግና ስራችንንም ከጨረስን በኋላ ወደ ዉጪ በማዉጣት ቤቱ አየር እንዲገባዉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስቷል፡፡

እሳት ስራ ላይ በሚዉልበት አከባቢ በቀላሉ ሊቀጣጠሉ የሚችሉ ተቀጣጣይ ነገሮችን ማራቅ፣ ማትም ሽቶና የመጥፎ ጠረን ማጥፊያ ወይም ተባይ ማስወገጃ ፍሊቶችን ከመርጨት መቆጠብ አስፈላጊ መሆኑን ያነሳዉ ኮሚሽኑ፣ በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ የተለያዩ መሳሪያዎች መሰኪያዎችን በአንድ ሶኬት ላይ ደራርቦ አለመጠቀም እንደሚገባ ገልጿል፡፡

ከበዓሉ መዝናናት ጋር ተያይዞ በየአከባቢዉ የሚዘጋጀዉ ካምፕ ፋየርም እሳት አደጋዎችን የሚያስከትል እንዳይሆን ህብረተሰቡ የበኩሉን ጥንቃቄ ማድረግ ፣ በተለይም ለእሳት አስጊ በሆኑ ተቋማትና በነዳጅ ዴፖዎች፣ በነዳጅ ማደያዎች እንዲሁም በመኖሪያ መንደሮች አከባቢ ጥንቃቅ ማድረግ አስፈላጊ ነዉ ብሏል፡፡

በተጨማሪም በዓሉን አስመልክቶ በሚደረገዉ መዝናናት በመጠኑም ቢሆን እንዲሁም መጠጥ ጠጥቶ መኪና ከማሽከርከር መቆጠብ ሊደርስ ከሚችለዉ የህይወትና ንብረት ዉድመት ራስን መጠበቅ መሆኑን ተገንዝቦ የጥንቃቄ እርምጃ መዉሰድ እንደሚገባዉ ነዉ ያስታወቀዉ፡፡

ህብረተሰቡ አቅሙ በፈቀደ መጠን እነዚህን የአደጋ መከላከል ጥንቃቄዎችን እያደረገ ከአቅም በላይ በሆኑ ሁኔታ እሳትና ሌሎች አደጋዎች ቢከሰቱ በአስቸኳይ የኮሚሽኑን ድጋፍ መጠየቅ ይኖርበታል ተብሏል፡፡

ኮሚሽኑ 24 ሰዓት ሙሉ ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ገልጾ፣ የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ቢከሰቱ አልያም ለአንቡላንስ አገልግሎት በ 939 ነጻ የስልክ ጥሪ መጠቀም እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *