የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልን የማደስ ስራ በ18 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል መታሰሩ ተገለጸ።

የእድሳት ስራው በ172 ሚሊየን ብር እንደሚከናወንም ተገልጿል።

ከ1936 ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከ80 ዓመታት በላይ ማገልገሉ ነው የተገለፀው ።

የእድሳት ስራው በሁለት ተከፍሎ እንደሚሠራ የተገለፀ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር የህንፃ ቤተክርስቲያኑ የእድሳት ስራ እንደሚከናወን እና ይህም በ172 ሚሊየን ብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ሁለተኛው ዙር የእድሳት ስራ ጊቢውን እና አጠቃላይ የጊቢውን መልክዓምድር የማሳመር እና ውበቱን እንደጠበቀ እንዲቆይ የማድረግ ስራ መሆኑ ተገልጿል።

በ3 ወር ውስጥ ጥናት በማካሄድ የካቴድራሉን የእድሳት ስራ ለመስራት ቢጀመርም የጥናት ስራው ብቻውን ወደ 2 አመት አከባቢ ፈጅቷል ነው የተባለው።

በተቻለ አቅም የእድሳት ስራውን ባጠረ ጊዜ በጥንቃቄ ለማከናወን ሲባል የጥናት ጊዜው መርዘሙ ነው የተገለፀው።

የሁለተኛውን ዙር የእድሳት ስራ ለመጀመርም ሰፊ ጥናት እየተደረገ መሆኑ እና የሚያስፈልገው የበጀት መጠንም እየተሰላ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶሱ የሚመራ ቢሆንም ግን እንደ ሌሎች ገዳማትና አድባራት ሁሉ በህዝብ ርዳታ እና ልገሳ የእድሳት ስራው እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ስልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ ናቸው።

ቅዱስ ሲኖዶሱ እስካሁን 10 ሚሊየን ብር ገቢ ማድረጉን ገልፀው የመላው የእምነቱ ተከታይ ርብርብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በእስከዳር ግርማ
ጥር 02 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.