ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎች እና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደባቸው፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በደንብ ማስከበር ባለስልጣን ቅንጅት በተከናወነ ኦፕሬሽን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎች እና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀ፡፡

ሺሻ የማስጨስ እና ጫት የማስቃም አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ የሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ እና በተለያየ መልኩ ባደረገው ጥናት መነሻነት በየካ፣ በቦሌ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ሺሻ በሚጨስባቸው ሆቴሎች እና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት በተከናወነ የኦፕሬሽን ስራ እርምጃ ተወስዷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደገለፀው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 እና ወረዳ 3 በተለያዩ አካባቢዎች በአጠቃላይ በ24 ሆቴሎች እና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ ጥር 7 ቀን 2015 ዓ/ም ከምሽት ጀምሮ ቁጥጥር የተደረገ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 8ቱ ሺሻ ሲያስጨሱ ተገኝተዋል፡፡

293 የሺሻ ዕቃዎች ከእነዚሁ ቤቶች ውስጥ የተያዙ ሲሆን አዋኪ ድርጊቱን ሲፈፅሙ እና ሲያስፈፅሙ የተገኙ 118 ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው በንግድ ቤቶቹ ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በቦሌ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች በተከናወነው የኦፕሬሽን በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ፍተሻ ካደረጉባቸው 23 ሆቴሎች እና የምሽት ጭፈራ ቤቶች መካከል በ7ቱ ላይ ሺሻ ሲጨስባቸው እንደተገኙ ተናግረዋል።

ከእነዚህ 7 ቤቶች ውስጥ 207 የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች እና በህገ ወጥ ተግባሩ ላይ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ 61 ግለሰቦች ተይዘው ጉዳያቸው በህግ አግባብ እየታየ እንደሚገኝ ምክትል ኢንስፔክተር አባይ ባህሩ ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 መገናኛ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆቴል ላይ በተደረገ ፍተሻ 86 የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች እና በአዋኪ ድርጊቱ ላይ ተሳትፈው የተገኙ 57 ግለሰቦች እንደተያዙ የክፍለ ከተማው ደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ሃላፊ ኮማንደር አስፋው የሺዳኜ ተናግረዋል፡፡

በህጋዊነት ሽፋን ህገ ወጥ ተግባር እንዲፈፀም በመፍቀድ በከተማችን ለሚከናወነው የፀጥታ ስራ እንቅፋት የሚሆኑ አንዳንድ ሆቴሎች፣ ባርና ሬስቶራንቶች ፣ የምሽት ጭፈራ ቤቶች እና መሰል የንግድ ተቋማት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ቀጣይነት እንዳለው የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ህብረተሰቡ መረጃ እና ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን እንዲያጠናክር ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥር 08 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *