የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ በቤተክርስቲያን ላይ ክህደት የፈጸሙ አካላት ወይም የሿሚና ተሿሚ ነን ባዮች ደመወዝ እንዲታገድና የሚገለገሉባቸው ቢሮዎችና ማረፊያ ቤቶች በአግባቡ እንዲጠበቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ጉባኤው በቤተክርስቲያን ላይ በተፈጸመው ሁሉን አቀፍ ክህደት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ ክህደቱን የፈጸሙት አካላት ሥልጣን የሰጣቸውን መዋቅር (ተቋም) በመካድ የፈጸሙት ድርጊት እጅጉን አሳዛኝ ነው ብሏል።
የተፈጸመው ጉዳይም ህገ ወጥና ቤተክርስቲያንን የማፍረስ ወንጀል ነው ያለው አስተዳደር ጉባኤው፤ በምንም መመዘኛ ይህን ከፈጸሙ አካላት ጋር መደራደር በተዘዋዋሪ የቤተክርስቲያናችንን ሕግና ሥራዓትን ማፍረስ ነው ሲል አስታውቋል።
በማያያዝም ጎሰኝነት ኑፋቄ መሆኑን የገለጸው አስተዳደር ጉባኤው፤ ይህን በመሰለ ተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ክህደቶች በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ተነቅፏል ካለ በኃላ በቋንቋ መማርና ማስተማር ችግር እንዳልሆነ በመረዳት ቤተክርስቲያን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ አባቶችን በመሾም አገልግሎት እንዲሰጡ ስታደርግ መቆየቷን ሕገ ወጥ ድርጊቱን ከፈጸሙ አካላት በላይ ማስረጃ አይኖርም ብሏል።
ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ አካል ሊሆኑ የሚችሉ የውሳኔ ሀሳቦችን ከቀኖና ቤተክርስቲያን እና ከሕግ አንጻር በመነሳት የጠቆመ ሲሆን፤ የተፈጸመው ክህደት ከቀኖና ቤተክርስቲያንና ከሕግ አንጻር እንዴት እንደሚገለጽ የሚያመለክት ሰፊ የሚዲያ ሥራ እንዲሰራ በመወሰንና በቂ ማብራሪያ የሚሰጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በመመደብ ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ቋንቋዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ ወስኗል።
ኹሉም የቤተክርስቲያኗ መዋቅር ተቋማቱን በንቃት መጠበቅና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚተላለፍ መመሪያን በትጋት መጠበቅ እንደሚገባና አስፈላጊው መመሪያ በአስቸኳይ እንዲተላለፍ የወሰነው አስተዳደር ጉባኤው በቤተክርስቲያን ላይ ክህደት የፈጸሙ አካላት ወይም የሿሚና ተሿሚ ነን ባዮች ደመወዝ እንዲታገድና የሚገለገሉባቸው ቢሮዎችና ማረፊያ ቤቶች በአግባቡ እንዲጠበቁ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ መንግሥትም እያደረገ ያለውን የቤተክርስቲያናትን ጥበቃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ጠይቋል።
ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናንና ምዕመናት ከጸሎት በተጨማሪ መዋቅራዊ መመሪያዎችን በትዕግስት እንዲጠብቁ አደራ በማለት የዕለቱን ስብሰባ በጸሎት ማጠናቀቁን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮ አፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም











