፭. በመግለጫው ፭ኛ አንቀጽ ላይ “…ሀገር ለማፍረስ በተለያዩ መንገዶች ሞክረው ያልተሳካላቸው ኃይሎች፣ ችግሩ እንዲባባስና እንዳይፈታ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑ ተደርሶበታል።” በማለት የተገለጸውን ፍሬ ሐሳብ በተመለከተ፡-
፭.፩. ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በማንኛውም ሁኔታ ሀገር የሚያፈርሱ ተግባራትን የምትጸየፍ፤ ዋነኛ ተልእኮዋም የሀገርን ሕልውና ማስቀጠል መኾኑን በተለያዩ የጦር ሜዳ ዐውዶች ላይ ታቦተ ሕጓን በማክበር ምእመናቶቿን ለትግል በመጥራት ጭምር የሀገርን ሕልውና ያስጠበቀች እና እያስጠበቀች ያለች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን መንግሥት በመግለጫው የገለጸው ዓይነት ተግባር ቢፈጸም የመጀመሪያ ተቃዋሚ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሆኗን በድጋሚ ማስታወስ ትወዳለች።
ለዚህም ማሳያዋ እያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ ፍጹም ሰላማዊ እና የሕግ አግባብ እና መሠረትን ብቻ ተከትላ እየፈጸመች መገኘቷ ነው፡፡
፭.፪. ችግሩ እንዳይፈታና እንዲባባስ የሚፈልጉት ሀገር አፍራሽ ኃይሎች ሕገ ወጥ ቡድኖች መሆናቸውን መንግሥት ጠንቅቆ የሚያውቀውና ልዩ ድጋፍም የሚሰጠው መሆኑን ቤተ ክርስቲያን እያሳወቀች መንግሥትም ሕገ ወጦችን ከመደገፍ እና ከማገዝ ተግባሩ እንዲቆጠብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በድጋሚ ታሳስባለች።
፭.፫. እንደ መግለጫው ከሆነ ችግሩ የሚፈታው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕልውናዋን፣ ሕጋዊነቷን፣ ተቋማዊ ነጻነቷን እና ከመንግሥት ልታገኝ የሚገባውን የሕግ ከለላ አጥታ ከሕገ ወጥ አካላት እኩል ስትታይ መሆኑን መግለጫው በግልጽ ቋንቋ ያስቀመጠ መሆኑን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጽኑ የምታወግዘው እና የምትቃወመው መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
፮. በመግለጫው የመጨረሻ አንቀጽ ላይ “..ችግሩን ለማባባስና በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር፣ ሀገርን ወደፈተና ለማስገባት በሚጥሩ አካላት ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን እንደሚሠራ በዚሁ አጋጣሚ ያሳውቃል” በማለት ያስቀመጠውን በተመለከተ፡-
፮.፩. ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል ከሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ አንስቶ እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር አልፎም እስከ ተከታይ ምዕመኖቿ ድረስ የሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም የሕዝቧ አንድነት እና የሕግ የበላይነት ጉዳይ ለድርድር እንደማታቀርብ በድጋሚ እያስታወስን ስልጣንን ተገን በማድረግ የቤተ ክርስቲያንችንን ሕጋዊ ጥያቄ በግድያ፤ በእስር፤ በማዋከብ እና በማስፈራራት ሊፈታ የማይችል ይልቁንም መንግሥት የተጣለበትን መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለ አድሎ መፈጸም ሲችል ብቻ መሆኑን ቤተ ክርስቲያናችን ዳግም በጽኑ ቃል ለማሳሰብ ትወዳለች፡፡
በመጨረሻም መንግሥት ይህንን መግለጫ ሲያወጣ በጥር ፳፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተፈጸመውን ሕገ ወጥ፤ አስነዋሪ እና ጭካኔ የተሞላበት የአደባባይ ግድያ እና የሕዝብ ፍጅት ያልጠቀሰና ሐዘኑን እንኳን መግለጽ ያልቻለበትና ያላወገዘ መሆኑን ስንመለከት የመንግሥትን ግልጽ ሚና በቀላሉ ለመረዳት እንድንችል ያደርገናል።
ስለሆነም መንግሥት ሕገ ወጥ አካላትን ድጋፍ ከመስጠት እና የእነርሱ ልሳን ሆኖ በመቅረብ የቤተ ክርስቲያንን ክብር እና ልእልና ከሚያንኳስስ ሕገ ወጥ ድርጊት እንዲታቀብ እያሳሰብን ሕገ ወጡ ስብስቦች እየፈጸሙ ላሉት ድርጊትም የሰጠውን ድጋፍ እና እገዛ በይፋ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ በመጠየቅ እንዲያቆም እናሳስባለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ጥር ፳፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ











