በሰሜኑ ጦርነት ምክነያት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ በዋግኽምራ ዞን በፃግብጅና አበርገሌ ወረዳዎች ከ71 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸዉ መመለስ እንዳልተቻለ የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች አስታዉቀዋል፡፡
የአበርገሌና የፃብግጂ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት፤ በፀጥታና በምግብ ዋስትና ችግር ከ71 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል ብለዋል፡፡
የአበርገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለሙ ክፍሌ የእርዳታ እጥረት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አካባቢዎቹ በህወሓት በታጣቂዎች የተያዙ በመሆናቸዉ ዜጎችን ወደ ቄያቸዉ መመለስ አልተቻለም ነዉ ያሉት፡፡
የፃብግጂ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሱ ደሳለኝ በበኩላቸዉ በመንግስት በኩል የሚደረገዉ እርዳታ በቂ አለመሆኑን ነግረዉናል፡፡
በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት የተደረገ ቢሆንም፣ ታጣቂዎቹ እስካሁን ሁለቱን ወረዳዎች ለቀው እንዳልወጡ የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች ነግረዉናል፡፡
ይህ ደግሞ ዜጎችን ቄያቸዉ ለመመለስ አዳጋች አድርጎባናል ብለዋል፡፡
በዚህም ምክንት ባለፈዉ ሳምንት ዞኑ ጻፍግጂ ወረዳ በወረዳዉ ታጣቂዎችና በህወሃት ሃይሎች መካከል ግጭት መከሰቱ ተሰምቷል፡፡
የወረዳዉ አስተዳዳሪ አቶ ንጉሱ ደሳለኝ በጉዳዩ ላይ በሰጡን ምላሽ ምላሽ ዜጎችን ወደ ቄያቸዉ ለመመለስ ሙከራ ሲደረግ ችግሩ እንደተከሰተ ነግረዉናል፡፡
መንግስት የጀመረዉን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርግ የጠየቁት የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች፤ አካባቢዎቹ ከታጣቂዎች ነፃ ከወጡ ዜጎችን መልሰዉ እንደሚያቋቋሙ አስታዉቀዋል፡፡
ከዚያ ባለፈ የምግብ ዋስትና ችግሩ ከፍተኛ በመሆኑ ከመደበኛዉ እርዳታ በተጨማሪ የረድኤት ተቋማትና በጎ አድራጊዎች እጃቸዉን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል፡፡
አሁን ላይ በዋግ ህምራ ዞን አበርገሌና ጻፍግጂ ወረዳዎች በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉና ከሁለት አመት በላይ የሆናቸዉ ከ71 ሺህ በላይ ዜጎች በሰቆጣ ከተማ ተጠልለዉ እንደሚገኙ ሰምተናል፡፡
በአባቱ መረቀ
የካቲት 07 ቀን 2015 ዓ.ም











