ህገ ወጥ የተሸከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ተቋማት መበራከታቸው ተገለፀ፡፡

በከተማዋ 163 ሺህ 434 ተሸከርካሪዎች በአምስት ወራት ውስጥ የተሸከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ እንደተደረገላቸው ተገልፃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሸከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ህጋዊ ፈቃድ ወስደው የተሸከርካሪን የቴክኒክ ብቃት ለማረጋገጥ እየሰሩ የሚገኙ የተሸከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ተቋማት ቢኖሩም በህገወጥ አሰራር ላይ የተሳማሩ አካላት መኖራቸውንም ገልጿል፡፡

ባለስልጣኑ በአምስት ወራት ውስጥ ከ56 የተሸከርካሪ ምርመራ ተቋማት ውስጥ 163ሺህ 434 በላይ ተሸከርካሩዎች የተሸከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ የተደረገ መሆኑን የባለስልጣኑ የድንገተኛ ተቋማት ብቃት ማረጋገጥ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ክንዳለም ጋሻው ገልፀዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በገለፃቸው ይህ ቁጥር በከተማዋ ላይ ካሉት ተሸከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ህገ-ወጦች በዚህ ዘርፍ መንሰራፋታቸውን አንስተዋል፡፡

በከተማዋ 56 ያህል የተሸከርካሪ ብቃት መመርመሪያ ተቋማት ያሉ ሲሆን ቢያንስ በወር 30 መኪና ቦሎ ያረጋሉ ተብሎ እንደሚታሰብና እነዚህ ተቋማት በስድስት ወራት ወስጥ ቢያንስ 190 ሺህ ተሸከርካሪዎችን ቦሎ ያረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡

በከተማዋ ከ700 ሺህ በላይ ተሸከርካሪዎች እንደሚገኙ የገለፁት ዳይሬክተሩ ይህ ጉዳይ ችግሩን ከባድ ያረገዋል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ተሸከርካሪዎቻቸውን ህጋዊ በሆኑ የቴክኒክ የምርመራ ተቋማት ብቻ እንዲያስመረምሩ አሳስበዋል፡፡

በአቤል ደጀኔ
የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.