ላለፉት 50 አመታት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ቦሌ ፋና ሸማቾች ማህበር መፍረሱን ኢትዮ ኤፍ ኤም በቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል፡፡
ከዚህ በፊት ይህ የህዝብ መዝናኛ ማዕከል የመፍረሱ ጉዳይ ለማህበራቱ በተነገራቸው ሰዓት ከወረዳው ጋር ውጥረት ውስጥ መግባታቸው አይዘነጋም፡፡
ከ4ሺህ 500 በላይ አባላት ያሉት ይህ ማህበር ከዚህ ማዕከል በተጨማሪም ሌሎች የመዝናኛ ማዕከላትን እያስተዳደረም ይገኛል፡፡
መዝናኛ ማዕከሉ በውስጡ የቴኒስ ሜዳዎችና የሠርግ አዳራሾች የነበረው ሲሆን፣ 17/19 መዝናኛ ማዕከል ብቻ 207 ሠራተኞች ነበሩት፡፡
የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች የሚካሄዱበት የፋና ፓርክ የሚተዳደረው በ17/23 የመዝናኛ ማዕከል ሥር ነው፡፡
ማዕከላቱ የሚገኙበት የቦሌ ወረዳ ሦስት የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ ፓርኮቹን ለሚያስተዳድረው ለቦሌ ፋና ሸማች በጻፈው ደብዳቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም መሬቱ እንዲሰጠው መጠየቁን አስታውቆ ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ ክፍለ ከተማ በፋና ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሥር የሚተዳደሩት 17/19 እና 17/23 መዝናኛ ማዕከላትን መሬት፣ ሞል፣ አፓርትመንት፣ እንዲሁም ለባለአምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ፣ ለኢንቨስተሮች ለመስጠት እንደሚፈልግ በደብዳቤው ጠይቆ እንደነበር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ደብዳቤው እንደሚያስረዳው የሁለቱ መዝናኛ ማዕከላት፣ መሬቱ የተፈለገው በኤምደብልዩኤስ (MWS) ትሬዲንግ ለሚገነባ ሞልና አፓርትመንት፣ እንዲሁም በበቀለ ለገሰና አገሩ አበበ ለሚገነባ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ነው ተብሏል፡፡
የማህበሩ አባላት ቦታው ማልማት ከተፈለገም የማልማት አቅም እንዳለቸው ተናግረው፣ የህዝብ መተንፈሻ የሆነን ማዕከል ማፈረስ ለህዝቡ አለማሰብ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቦሌ ሸማች መዝናኛ ማዕከል ፊት ለፊት አስገንብቷቸው የነበሩ ሱቆች እንዲሁም ለህዝቡ አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ አዳራሾች እየፈረሱ እንደሚገኙ አትዮ ኤፍ ኤም ቦታው ድረስ ተገኝቶ አረጋግጧል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም ማዕከላቱ የሚገኙበት የቦሌ ወረዳ ሦስት የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ለማግኘት የወረዳው ሃላፊዎችን በስልክ ለማግኝት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረግን ቢሆንም ሊሳካልን አልቻለም፡፡
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም











