የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በፕላስቲክ አሰባሰብ ዙሪያ አስገዳጅ ህግ እያዘጋጀ መሆኑን ገለጸ፡፡

አስገዳጅ ህጉ በሚጣሉ የዉሃ እና የስላሳ መጠጦች ማሸጊያ ፕላስቲኮች አሰባሰብ ላይ ያተኮረ መሆኑም ታውቋል፡፡

የባለስልጣኑ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ዳይሬክተር ጀነራል ግርማ ገመቹ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት እነዚህን የሚጣሉ የዉሃ እና ለስላሳ ማሸጊያ ፕላስቲኮችን በአገራችን እንደገና ለመጠቀም የሚያስችል አቅም ባለመኖሩ ባለፉት 5 ዓመታት ፕላስቲኮቹን በመሰብሰብ ፈጭቶ ወደ ዉጭ አገራት የመላክ ስራ እየተሰራ መሆኑን ነግረዉናል፡፡

እስካሁን ድረስ በዓመት ወደ 973 ሺህ ቶን አዳዲስ የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን ወደ አገር ዉስጥ እናስገባለን ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ወደ ዉጭ ተፈጭቶ የሚላከዉ ግን ከ40ሺህ ቶን አይበልጥም፤ ይህም ከ5 በመቶ በታች ሲሆን በጣም ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህንን ለማስተካከል የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸዉ አካላት ማስረከቡን የገለጹት አቶ ግርማ፣ አስገዳጅ የሆነ ህግም በቅርብ እንደሚወጣ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ባለዉ አሰራር አስገዳጅ ነገር የለዉም የሚሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ፣ በቅርቡ መስሪያ ቤታቸዉ የማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን ቀለም መቀየሩን አስታዉሰዉ፣ አምራች ድርጅቶችም ከ10 ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ፣ ፕላስቲክን ተጠቅሞ ምርታቸዉን ማሸግ እንዲቀንሱ እና ወደሌላ የምርት ማሸጊያ እንዲገቡ የሚያደርግ ስትራቴጂ መኖሩን እና ይህንንም ማድረግ የሚቻለዉ አሁን ያሉ ህጎች ወደ ስራ ሲገቡ ነዉ ብለዋል፡፡

ህጉ ሁለት ስልት አለዉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ አንደኛዉ ራሳቸዉ በሚያቋቁሙት ማዕከላት ያመረቱትን እንዲሰበስቡ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሌላዉ ደግሞ የሚጣል ፕላስቲክን መሰብሰብ አልያም ለሚሰበስቡ ማዘጋጃ ቤቶች መስጠት እንደሚሆን አንስተዋል፡፡

የሚያመርቱት የምርት መጠን መወገድ ያለበት እና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተዘጋጀዉ መጠን ሁሉ ስለሚታወቅ ወደ አስገዳጅ ማዕቀፎች እንደሚገባም ነግረዉናል፡፡

የህግ ማዕቀፉ በሚኒስቴሮች ምክርቤት ዉይይቶች የተካሄዱበት ሲሆን ቀሪ ዉይይቶች ከተደረጉ በኋላ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በእስከዳር ግርማ

የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *