በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን በደረሰ የጎርፍ አደጋ 13 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡

በደቡብ ክልል፤ ኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ፤ የ13 ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ተናግረዋል።

የኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊው አቶ ሰራዊት ዲባባ “ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ እንስሳት” በጎርፍ መወሰዳቸውን አክለዋል።

ትናንት ሐሙስ መጋቢት 7፤ 2015 ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ በጣለው ከባድ ዝናብ፤ በሰገን ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ ሰገን ዶዴ እና መገርሳ ወንዞች ሞልተው የጎርፍ አደጋ መከሰቱን አቶ ሰራዊት ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር ገልጸዋል።

በአደጋውም በገርጨ እና አይሎታ ደካቱ ቀበሌ ነዋሪዎች የሆኑ 13 ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

“ከትላንት ከሰዓት ጀምሮ በጎርፍ መወሰዳቸውን በአጠገባቸው ከነበሩ ሰዎች አረጋግጠናል። ለማዳን ቢሞከርም አልተቻለም” ሲሉ ከአደጋው በኋላ ህይወት ለማትረፍ የተደረገውን ጥረት አስረድተዋል።

በአደጋው ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል ሁለቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን አቶ ሰራዊት አስታውቀዋል።

ከትላንቱ የጎርፍ አደጋ በኋላ በአካባቢው በተደረገ አሰሳ፤ እስካሁን ድረስ ማግኘት የታቸለው የአራት ሰዎች አስክሬን ብቻ መሆኑም የመምሪያ ኃላፊው ገልጸዋል።

የቀሪዎቹ ዘጠኝ ሰዎች አስክሬን ፍለጋ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መጋቢት 08 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.