በአዲስ አበባ ከተማ 161 ቦታዎች ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ 161 ቦታዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው በሚል መለየታቸውን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ለሁሉም ክፍለ ከተሞች የአደጋ መከላከል ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን ያስታወቀ ሲሆን፣ በነዚህ ቦታዎች የሚገኙ ዜጎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወሩ ተጠይቋል ብሏል፡፡
የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ በኢትዮ ኤፍ ኤም ለሚተላለፈው የቸገረን ነገር ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፣ ወቅቱ የበልግ ዝናብ የሚጥልበት ጊዜ በመሆኑ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
የአደጋ መጠኑ በክፍለ ከተሞች ደረጃ የሚለያይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ንጋቱ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ችግሩ የባሰ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመዲናዋ ከሰሞኑ በደረሰው የጎርፍ አደጋ አራት ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን ሶስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በየካቲት ወር ብቻ በአዲስ አበባ ደረጃ 42 የእሳት አደጋዎች መድረሳቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም











