ጠቅላይ ሚንስትሩ ለፓርላማ ማብራሪያ ሊሰጡ ነው!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች፤ ነገ በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያ ሊሰጡ መሆኑ ታውቋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ማክሰኞ መጋቢት 19፤ 2015 በሚኖረው መደበኛ ስብሰባው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎችን የሚሰጡትን ምላሽ እና ማብራሪያ እንደሚያዳምጥ እና የፓርላማ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ያስገቡት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መሆኑን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል፡፡

ከአንድ ወር ዕረፍት በኋላ የተመለሱት የፓርላማ አባላቱ፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 9፤ 2015 በተወካዮች ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በነበራቸው ስልጠና ይኸው እንደተነገራቸው ምንጮቹ ገልጸዋል።

ይህንኑ ያረጋገጡት አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፓርላማ አባል፤ “ ‘በአስቸኳይ አስገቡ’ ብለው ባለፈው ቅዳሜ ነገሩን። ቀን ላይ ነግረውን፤ ‘እስከ ማታ ድረስ’ አሉን” ሲሉ ለጥያቄ ማቅረቢያ የተሰጠው አጭር ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።

የፓርላማ አባሉ አክለውም፤ “ብዙዎቻችን ‘አይሆንም፤ ተረጋግተን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርብ አይነት ጥያቄ በአግባቡ ማዘጋጀት አለብን’ ስንል እስከ እሁድ አመሻሽ ድረስ አቅርቡ ተባለ” ሲሉ ጥያቄ የማቅረቢያ ጊዜው በአንድ ቀን እንዲራዘም መደረጉን አስረድተዋል።

በዚህ አካሄድ እስከ ባለፈው ሳምንት እሁድ አመሻሽ ድረስ፤ የፓርላማ አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች አስገብተው ማጠናቀቃቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

በነገው ዕለት በሚካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል፤ “የኑሮ ውድነትን የተመለከቱ ይኖራሉ” ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ጠቁመዋል። “ወደ አዲስ አበባ አትገቡም እየተባለ ወደ አማራ ክልል የሚመለሱ ሰዎች” ጉዳይን የተመለከቱ ጥያቄዎችም፤ በነገው የፓርላማ ስብሰባ ጥያቄ ሊቀርብ እንደሚችል ምንጮች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.