ማስተርካርድ ፋውንዴሽን እና “ገበያ” የሥራ ፈጣሪዎችን አቅም የሚጨምር አዲስ ፕሮግራም ጀመሩ፡፡

ሶፍትዌርን እንደ አገልግሎት የሚሰጠው እና በመላው አፍሪካ የሚንቀሳቀሰው ገበያ እና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ለአምስት አመት የሚቆይና ለመቶ ሥራ ፈጣሪዎች ቁርጥ ሥራዎችን ወይም ጊዜያዊ ሥራዎችን የሚያገናኙ የገበያ ፕላትፎርሞችን የሚያቀርብ ‹‹መሥራት›› የተባለ ፕሮግራም አስተዋውቀዋል።

“ቁርጥ ሥራ” ወይም “ጊዜያዊ ሥራ” የሚለው ጊዜያዊ ሥራዎችን፣ የትርፍ ጊዜ ሥራዎችን፣ የኮንትራት ሥራዎችን፣ ተደጋጋሚም ቢሆኑም መደበኛ ቅጥርን መሠረት ያላደረጉና በስምምነት ቁርጥ ክፍያ የሚፈጸምባቸው ሥራዎችን እና የመሳሰሉትን ሁሉ የሚያመለክት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች አጋሮቻቸው የጋራ ልምዳቸውን ለፕሮግራሙ የተመደበዉን 48 ሚሊዮን ዶላር በመጠቀም የገበያዉን ሞዴል በቱሪዝም እና ሆቴል፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በጤና፣ በንግድ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በፕሮፌሽናል አገልግሎቶች፣ በትራንስፖርት፣ እንዲሁም በመዝናኛ ዘርፎች ላይ ወደ መቶ የሚጠጉ ፕላትፎርሞችን ለመፍጠር አብረው እንደሚሰሩም ነዉ የተገለጸዉ፡፡

ይህ ትብብር ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ወጣቶችን በልዩ ልዩ ሥራዎች የማሰማራት እስትራቴጂ (“Young Africa Works Strategy”) ጋር አብሮ የሚሄድ ነዉ የተባለ ሲሆን ለሁለት ሚሊየን ወጣቶች ገበያና ሥራ የማፈላለግ ክህሎት የሚያስጨብጥ ሆኖ አንድ ሚሊየን የሚሆኑት (70 ከመቶ ሴቶች) ሥራ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ከድርጅቱ መሥራቾች አንዱ የሆኑት አማዱ ዳፌ፣ “ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው፤ የፕሮግራሙ አካል በመሆናችንም እጅግ ደስተኛ ነን” ሲሉ ስለ አጋርነቱ አስተያየት ሰጥተዋል። “የገበያ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ በመላው አፍሪካ ልዩ ልዩ ቁርጥ ሥራዎችን የሚያስተናግድ ኢኮኖሚ እንዲለመድ ነገሮችን ማፋጠን ነው” ሲሉም አክለዋል።

የመሥራት ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት መና ታፈሰ ደግሞ፣ “ሴቶች እና ወጣቶች ሁሌም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወቱ ነበር” ያሉ ሲሆን፣ “አሁን በኢትዮጵያ የስራና ቅጥር ሁኔታ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያሉንን ግብአቶች ሁሉ በመጠቀም እነሱን እንደዋና የለውጥ ኃይል ለመጠቀም ቆርጠን ተነሥተናል” ብለዋል።

በእስከዳር ግርማ

መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.