ዶ/ር ጫላ ዋታ ያለ መከሰስ መብታቸው እንደተነሳ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ጉባኤ፤ ያለ መከሰስ መብታቸውን ያነሳባቸው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጫላ ዋታ) በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡

የምክር ቤት አባሉ ያለ መከሰስ መብታቸው የተነሳው ፍትሕ ሚኒስቴር በሙስና ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው፡፡

አባሉ የመንግሥት ግዥ ሕግ ከሚፈቅደው ሕግ ውጪ፣ በግላቸው ለመሰረቱት ቢ ኤች ዩ ኮንሰልታንስ የተባለ የንግድ ድርጅት በግንባታ አማካሪነት በመቅጠር በቀጥታ ግዥ በመፈጸም በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል፡፡

በተደረገባቸው ምርመራ ከ23 ሚሊየን ብር በላይ ከዩኒቨርሲቲው አካውንት ወደ ድርጅቱ ያለአግባብ ገቢ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ 195 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያለ አግባብ ግዥ እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተረጋግጧል ተብሏል።

በተጨማሪም በ116 ሚሊዮን ብር በግል ተቋራጭ ሥም 14 ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪዎች እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

በዩኒቨርስቲው ገንዘብ የተገዙ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ባለቤትነታቸው በግል ድርጅት ሆኖ መገኘቱም ተመላክቷል፡፡

ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ጫላ ዋታ ለምክር ቤቱ በሰጡት የመከራከሪያ ሃሳብም፤ ቢ ኤች ዩ ኮንሰልታንስ የዩኒቨርሲቲው የገቢ ማመንጫ ድርጅት ነው ማለታቸውን የአዲስ ማለዳ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ ዛሬ ያካሄደውን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ሲያጠናቅቅ፤ ያለ መከሰስ መብታቸው የተነሳባቸ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጫላ ዋታ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.