የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገድ ብቻ መሆኑን ተከትሎ ህገወጥ የነዳጅ ንግድ መበራከቱን የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡
ህገወጥ ንግዱ ተጠናክሮ ቢቀጥልም የነዳጅ ፍላጎቱ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በብላክ ማርኬት እንኳን ነዳጅ በበቂ ማግኘት እንዳልተቻለ ነዉ የነገሩን፡፡
ነዳጅ ማደያዎች አካባቢ ያለዉ ሁኔታ የተጨናነቀ በመሆኑ እና ሰልፎች መቀነስ ካልቻሉ በጊዜ ብዛት ህገወጥ ንግዱ እየተስፋፋ ይሄዳል ነዉ ያሉት፡፡
ነዳጅ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ብቻ መሆኑ የፈጠረዉ ድንገታዊ መጨናነቅ ሲስተሙን እንዲዘገይ አድርጎታል ያሉት አቶ ኤፍሬም ከቀን ቀን መሻሻል እያሳየ መሄዱ የማይቀር ቢሆንም የተፈጠረዉን ችግር ግን እንደቀልድ መወጣት የምንችለዉ አይደለም ብለዋል፡፡
ደንበኞች መጨናነቁን ለመሸሽ በሚል በተገኘዉ ታንከር ሁሉ ነዳጅ ቀድቶ የመሄድ ሁኔታ በመኖሩ በነዳጅ ማደያዎች ዉስጥ ያለዉን የነዳጅ ክምችት በአንድ ጊዜ ዉስጥ እንደሚጨርሰው የተናገሩት አቶ ኤፍሬም በዛዉ ልክ አቅርቦት ከሌለ ሰልፉ እና መጉላላቱ እየጨመረ ይሄዳል ብለዋል፡፡
ቀድሞም ችግሩ እንደነበር የነገሩን አቶ ኤፍሬም በበዓላት ወቅት የነበረዉ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም እንደ አንድ ምክንያት የሚነሳ ጉዳይ መሆኑን አንስተዉ በጅቡቲ መስመር ላይ የነበሩ ችግሮችም ባሉበት ሁኔታ ላይ የተጨመረዉ ይህ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሁኔታዉን የባሰ አድርጎታል ነዉ ያሉት፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ አሁን ላይ በዚህ የነዳጅ አቅርቦቱ እንኳን አስተማማኝ ባልሆነበት ጊዜ ላይ መጀመሩ ጊዜዉን የጠበቀ አለመሆኑን አንስተዉ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ሲሉ አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ የነዳጅ እጥረት መኖሩን የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ እየጨረሱ ስራ እያቆሙ መሆናቸዉን እና ብዙ መኪኖችም ነዳጅ ይመጣል በሚል ተስፋ ሰልፋቸዉን ይዘዉ እዛዉ ቆመዉ እያደሩ መሆናቸዉን ነዉ የነገሩን፡፡
በመጨረሻም የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ሚና የለየ አይደለም ያሉት አቶ ኤፍሬም ቀድመዉ ሲስተም ዉስጥ የገቡት ለህብረተሰቡ አገልገሎት የሚሰጡ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ጭምር በዚህ አሰራር እየተጉላሉ መሆኑን አንስተዉ ይህ ተገቢ አለመሆኑን ነዉ የገለጹት፡፡
እስከዳር ግርማ
ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም











