ሼክ ካደር የተሰኘው ፍልስጤማዊ ከ86 ቀናት የረሃብ አድማ በኋላ ዛሬ ማለዳ ህይወቱ ማለፉን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል፡፡
ግለሰቡ በእስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አመራርና አቀንቃኝ እንደነበር መረጃው ጠቅሷል፡፡
የ45 አመቱ የ9 ልጆች አባት የሆነው ይህ ግለሰብ የእስራኤልን ህገ-ወጥ ወረራ ሲታገል መታሰሩን ተከትሎ የካቲት 5 የረሃብ አድማውን እንደጀመረ ሚድል ኢስት ሞኒተር አስነብቧል፡፡
ይሁንና ግለሰቡ ከ86 ቀናት የረሃብ አድማ በኋላ በእስራኤል “ኒትዛን” እስር ቤት ውስጥ ራሱን ስቶ የተገኘ ሲሆን ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ህይወቱ ማለፉ ታውቋል።
በእስራኤል የኒትዛን እስር ቤት አስተዳደር በበኩሉ “ለግለሰቡ ሞት ተጠያቂ አይደለሁም፤ግለሰቡ የህክምና ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም” ብሏል፡፡
የዌስት ባንክ ጉዳይ በሁለቱ ሃገራት መካከል ከፍተኛ ውዝገብን ሲፈጥር የቆየና ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነ ሲሆን አሁንም ድረስ መፍትሄ እንዳላገኘ ዘገባው ጠቅሷል፡፡
በመሳይ ገ/መድህን
ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም











