በዋግህምራ ያሉ መጠለያ ካምፖች እየፈረሱ ነዉ፡፡

በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ያሉ መጠለያ ካምፖች ስደተኞች ወደ ወረዳቸዉ በመመለሳቸዉ እየፈረሱ መሆኑን ኢትዮ ኤፍኤም ሰምቷል፡፡

ካለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በካምፑ ዉስጥ ምንም ዓይነት ስደተኞች የሉም ያሉት የዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ምህረት መላኩ፣ ከትናንት ወዲያ ጀምሮ መጠለያ ካምፖቹ መፍረስ መጀመራቸዉን ገልጸዋል፡፡

አጎራባች ወረዳዎቹ ነጻ በመሆናቸዉ ስደተኞቹን ወደ ወረዳዎቹ መልሰናል ያሉት አቶ ምህረት፣ የመመለስ ስርዓቱ ከ20 ቀናት በላይ የፈጀ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ከ 66ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በመጠለያ ካምፖች ዉስጥ ነበሩ፣ነገር ግን አሁን ላይ ሁሉም ወደ ወረዳቸዉ ተመልሰዋል፣መጠለያ ካምፖቹንም እያፈረስን ነዉ ብለዉናል፡፡

መጠለያ ካምፖቹን የሰሩት ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች አፍርሰዉ ለመንግስት እንዲያስረክቡ መልዕክት ማስተላለፋቸዉን የገለጹት አቶ ምህረት ከትናንት ወዲያ ጀምሮም ካምፖቹ እየፈረሱ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ከፍተኛ ተፈናቃዮች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች አንዱ ሲሆን በብዛት ደግሞ በዋግህምራና ደብረ-ብርሃን እንዲሁም በሌሎችም አካባቢዎች ተፈናቃዮች እርዳታ እየተጠባበቁ እንደነበር ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.