በግሉ የጤና ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለሕብረተሰቡ በፋይናንስ ተደራሽ እንዲሆኑ የአሠራር፣ የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያ ያስፈልጋል….ኢሰመኮ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የግሉ የጤና ዘርፍ ከሕብረተሰቡ የመክፈል ዐቅም ጋር የተመጣጠነ እና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት አቅርቦት ላይ ያተኮረ ባለ 39 ገጽ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ¬¬¬ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

የጤና መብት ተገኝነት፣ ተደራሽነት፣ ተቀባይነት እና ጥራት ላይ ያተኮሩ አራት ዋና ዋና ይዘቶች ያሉት ሲሆን ክትትሉ በተደራሽነት (accessibility) ሥር ከተጠቃለሉት ንዑስ ይዘቶች መካከል በገንዘብ ተደራሽነት ላይ ትኩረት በማድረግ መከናወኑ በሪፖርቱ ተብራርቷል።

ሪፖርቱን ለማዘጋጀት በአጠቃላይ ከ218 የባለድርሻ አካላት (80 የግል የጤና ተቋማት ኀላፊዎች፣ 8 መንግሥታዊ ያልሆኑ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ተጠሪዎች፣ 20 የመንግሥት ተቋማት ኀላፊዎች፣ 80 የግል የጤና ተቋማት ተጠቃሚዎች/ተገልጋዮች እና 30 የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች) ከሃዋሳ፣ ከባሕር ዳር፣ ከአዲስ አበባ እና ከጅማ ከተሞች መረጃዎች ተሰብስበዋል።

የግሉ የጤና ዘርፍ አገልግሎት ከመንግሥት የጤና ዘርፍ አገልግሎት አንጻር ሲታይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሕብረተሰቡ የመክፈል ዐቅም በላይ እየሆነ መምጣቱ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ለዚህም ዋነኛ ምክንያቶች የሕክምና ግብዓቶች አቅርቦት እጥረት እና ዋጋ መናር፣ የግዴታ ግዥ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እና ቁጥጥር አናሳ መሆን፣ ከሙያ ሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ተግባራት እና በመንግሥት ተቋማት የተሟላ እና አመርቂ አገልግሎት አለመኖር መሆናቸውን ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ ጠቅሷል።

ኢሰመኮ የጤና መብት በተሻለ ሁኔታ እንዲተገበር እና ቀደም ሲል የተዘረዘሩትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ይረዳሉ በማለት የለያቸውን የአሠራር፣ የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦችን በሪፖርቱ አቅርቧል።

ከእነዚህምመካከል በሕዝብ የጤና ተቋማት ላይ የአገልግሎት እና የአቅርቦት ማሻሻያ እና ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ሕብረተሰቡ አማራጭ እንዲያገኝ ማድረግ፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድኅን አገልግሎት ማስፋፋት እና የግል የጤና ተቋማትም የሚሳተፉበትን አሠራር መዘርጋት፣ የመንግሥት እና የግል የጤና ተቋማት ሽርክናዎችን (public-private partnerships) ማጠናከር የሚሉት በምክረ ሐሳብነት በሪፖርቱ ተካተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአብዛኛው በመንግሥት ሲቀርብ በነበረው የጤና አገልግሎት ላይ የግሉ ዘርፍ በሰፊው መሰማራቱ ሊበረታታ እንደሚገባው ገልጸው፣ ተቋማቱ ካላቸው የፋይናንስ ተደራሽነት አንጻር ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ አስረድተዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም የግል የጤና ተቋማት ለሕብረተሰቡ በገንዘብ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል እና የጤና መብትን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ግዴታ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሰኔ 05 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.