ዊንጉ አፍሪካ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነዉን የዳታ ማዕከል በICT ፖርክ በዛሬው እለት አስመርቋል።

ዊንጉ አፍሪካ ለአስራ ሁለት ዓመታት በሴክተሩ ላይ መቆየቱም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከጅቡቲ፣ታንዛንያ እና ሱማሊላንድ በመቀጠል አራተኛዋ መዳረሻዉ መሆኗንም ነው ዊንጉ የገለጸው።

የዊንጉ አፍሪካ የኢትዮጵያ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ወርቁ የዳታ ማዕከሉ ለተለያዩ ተቋማትን የዳታ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት የድርጅታቸዉን የዳታ ማዕከል በዊንጉ በማድረግ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ነው የተናገሩት፡፡

ሀገራችን እየተከተለችዉ የሚገኘዉን የ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በ2025 ለማሳካት ለምታደርገዉ ትግበራ ዋነኛ አጋዥ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

የዳታ አገልግሎት እንደሚሰጥ የተገለፀዉ ድርጅቱ፣ ከአሁኑ የተለያዩ የሀገራችን የባንክ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑንም አቶ ተሾመ ገልፀዋል።

በዚህም እንደ ሳፋሪኮም፣አቢሲኒያ ባንክ እና ሀይብሪድ ዲዛይንን (ራይድን) ጨምሮ ወደ ስምንት የሚሆኑ የሀገራችን የዲጂታሌ ሴክተሩ ላይ በስፋት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የICT ፖርክ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሄኖክ አህመድ በበኩላቸዉ፣ የዲጂታል ኢኮኖሚዉን ለማሳደግ እንደ ICT ፓርክ ያሉ ተቋማት ሚናቸዉ ከፍ ያለ ነዉ ብለዋል።

የተለያዩ ተቋማትም በዚህ ፓርክ ኢንቨስተ እያረጉ ነዉ ያሉ ሲሆን፣ ዊንጉ አፍሪካ ከአሁኑ ደንበኞች እያፈራ ያለ ትልቅ ተቋም ነዉ ብለዋል፤ ፖርኩም ወደ አራት የሚሆኑ የዳታ ማዕከላት በዉስጡ የያዘ መሆኑን ገልፀዋል።

የዊንጉ አፍሪካ የዳታ ማዕከልን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ከግማሽ የፈጀ ሲሆን አጠቃላይ ወጪዉም ከሀምሳ ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ኢትዮ ኤፍ ኤም በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ከተደረጉ ገለጻዎች ሰምቷል፡፡

በአቤል ደጀኔ

ሰኔ 06 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.