ለዚህ ዓመት የሃጅ ተጓዦች 15 ሚሊየን ዶላር መሰጠቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገለጸ፡፡

ባለፈው አመት የተሰጠው 8 ሚሊየን ዶላር እንደነበር ባንኩ አስታውሷል፡፡

ባንኩ ይህን በማስመልከት በዛሬው ዕለት ለሃጅ እና ኡምራ ተጓዦች የሚሆን የለበይክ ሂሳብን የማስተዋወቅ እና ሂሳብ የማስከፈት ንቅናቄ ማስጀመሪያ ፕሮግራም አዘጋጅቷል።

በ3ኛው ዙር ሃጅ ለሁሉም የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የተገኙት የባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ኑሪ ሁሴን፣ በአገራችን ያለው የነፍስ ወከፍ ገቢ ዝቅተኛ በመሆኑ ብዙዎች በአንድ ጊዜ ክፍያ የሃጅ ስነ-ስርዓትን ለመፈፀም ይቸገራሉ ብለዋል።

ይህ በመሆኑም አማኞች በረጅም ጊዜ ቁጠባ የሃጅና ኡምራ ጉዞ እንዲያደርጉ የሚያስችል የባንክ ሂሳብ መክፈት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አንስተዋል።

የሸሪዓ መርህን መሠረት ያደረገው የለበይክ የቁጠባ ሂሳብ፣ በፈረንጆቹ 2019 ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ 80 ሺህ 8መቶ 13 ደንበኞችን ያፈራና 773 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ቁጠባ የተካሄደበት መሆኑን ገልጸዋል።

ባንኩ ባለፉት 10 ዓመታት የሸሪዓ መርሆችን የተከተሉ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ በአሁኑ ጊዜ ከ6 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ማፍራት የተቻለ መሆኑንና እስከ 90 ቢሊየን ብርም ተቀማጭ ማሰባሰብ መቻሉን አንስተዋል።

ባንኩ 1 ሺህ 9 መቶ 15 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 1 መቶ 47 ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም በፕሮግራሙ ላይ ከተደረጉ ገለጻዎች ሰምቷል።

በእስከዳር ግርማ

ሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.