ስለ ጸረ-አበረታች መድሃኒት የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው ተባለ፡፡

ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለ አበረታች መድሃኒት ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲያድጉ የሚያደርግ የትምህርት ስርዓት ተዘርግቶ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመም ባለስልጣን አስታውቋል።

በያዝነው አመት የተጀመረው የትምህርት ስርዓት፣ ከአምስተኛ ክፍል በላይ ለሆኑ ተማሪዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል ተናግረዋል።

የአበረታች ቅመሞች የግንዛቤ ትምህርት ለተማሪዎች ለብቻው የሚሰጥ ሳይሆን፣ እንደ አይነቱ በተለያዩ የትምህርት አይነቶች ተካቶ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ስርዓቱ ተማሪዎች ከልጅነታው ጀምሮ የአበረታች መድኃኒት ጎጂነትን በመረዳት፣እራሳቸውን ከጤና እክል እንዲጠበቁ እና በራሳቸው አቅም የሚተማመኑ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡

ከአበረታች መድኃኒት የፀዳ እና በራሱ አቅም የሚተማመን ስፖርተኛን ለመፍጠር ግንዛቤን በትምህርት መልክ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቱ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ መደረጉን ባለስልጣኑ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።

ተቋሙም ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲያስችለው የአቅም ግንባታ አደረጃጀትን የማጠናከር እና የሰው ሃይል የማብቃት ስራን እየሰራ መሆኑን አንስቷል።

አበረታች ቅመም የአንድን ሃገር ስፖርት እና ክብር ያበላሻል ያለው ባለስልጣኑ ይህንን ለመከላከል በጋራ እንስራ ሲልም ጠይቋል።

በዚህ አመት 7 አትሌቶች በአበረታች ቅመም ተጠርጥረው አራቱ በባለስልጣኑ፣ የተቀሩት ሶስቱ ደግሞ በአለምአቀፍ አትሌቲክስ ፌደሬሽን መያዛቸው ተገልጿል፡፡

በመሳይ ገ/መድህን

ሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *