“አውደ-ርዕዩ በህክምናው ዘርፍ በምን ደረጃ ላይ እንደምንገኝ የሚያሳይ ነው” የጤና ሚንስቴር ዴኤታ—ዶ/ር ደረጀ ድጉማ

ለአንድ ወር ይቆያል የተባለው ብሔራዊ የጤና አውደ-ርዕይ በትላንትናው ዕለት በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል፡፡

በዚህ የጤና አውደርዕይ ላይ የተለያዩ ሃገር በቀል ህክምና ፣ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና ፣ የሆስፒታል አገልግሎት፣ የጤና ሳይንስ ትምህርትና ስልጠና፣ ድንገተኛ ምላሽ አሰጣጥ ፣ የጤና የፈጠራ ግኝቶች፣ የህክምና ቁሳቁስ እና የመድሃኒት ምርት እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳዩ ስራዎች በአውደ-ርዕዩ ላይ ቀርበዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ደረጄ ድጉማ የተዘጋጀው የጤና አውደ-ርዕይ ከዚህ ቀደም በዚህ መልኩ ተዘጋጅቶ የማያውቅ ከመሆኑም ባሻገር በህክምናው ዘርፍ ያውን የዕውቀት ክፍተት ለማየትና ለመሙላት እድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአውደ-ርዕዩ ላይ የተለያዩ የግል ድርጅቶችም እየተሳተፉ እንደሚገኙ ኢትዮ ኤፍ ኤም ተመልክቷል፡፡

ድርጅቶቹም አውደ-ርዕዩ ያላቸውን አገልግሎቶች ለብዙሃኑ ለማስተዋወቅና ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ለማስተዋወቅ መልካም እድል ይፈጥርልናል ብለው እንደሚያምኑ ነግረውናል፡፡

አገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕዩ ላይ በዋናነት ከዚህ ቀደም ታማሚዎች ወደ ውጪ ሄደው ህክምና እንዲያገኙ ያስገድዱ ከነበሩ የህክምና መሳሪያዎች ውስጥ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡትን ለማሳወቅ እና ህክምናው ያለበትን ደረጃም የሚሳይ መሆኑንም ሚንስቴር ዴኤታው ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል፡፡

ትናንት በነበረው የአውደ-ርዕዩ መክፈቻ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ ሌሎችም ባለስልጣናት ጉብኝት ማድረጋቸው ይተወሳል፡፡

በረድኤት ገበየሁ

ሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም

ፎቶ-ሶሽያል ሚዲያ

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.