የለሜቻ ግርማ እና ጃኮብ ኢንጌብሪግስቴን ፍልሚያ ትኩረት ስቧል፡፡

በኳታር ዶሃ ተጀምሮ በ14 የተለያዩ ከተሞች ከተካሄደ በኋላ ፍፃሜውን በአሜሪካ ዩጂን ኦሬጎን ፍፃሜውን የሚያደርገው ተወዳጁ የዳይመንድ ሊግ ዛሬ ስድስተኛው ዙር በስዊዘርላንድ ሉዛን ይደረጋል፡፡

በርካታ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሜዳሊስቶች ይሳተፉበታል፡፡ በምሽቱ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ውድድሮች ይደረጋሉ፡፡

በስታድ ኦሎምፒክ ደ ላ ፖንታይስ (Stade Olympique de la Pontaise) በሚደረገው የምሽቱ የዳይመንድ ሊግ ፍልሚያ በተለይም ደግሞ በ1500 ሜትር ኖርዌጂያዊው ጃኮብ ኢንጌብሪግስቴን እና ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ የሚያደርጉት ፉክክር ከምንግዜውም በላይ የብዙዎቹን ቀልብ የሳበ ሆኗል፡፡

በተመሳሳይ የ22 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙት ሁለቱ አትሌቶች በዚህ ወር ታላላቅ ገድሎችን ፈፅመዋል፡፡

ኢንጌብሪግስቴን ባለፈው የካቲት ወር የቤት ውስጥ 1500 ሜትር አዲስ የዓለም ሪከርድ (3:30.6) መስበሩ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ወር ደግሞ በፓሪሱ ዳይመንድ ሊግ ላለፉት 26 ዓመታት በኬንያዊው ዳንኤል ኩመን ተይዞ የቆየውን የ2 ማይልስ የዓለም ሪከርድ (7:54.10) ሰብሯል፡፡

ለሜቻ ደግሞ በቅርቡ በ3000 ሜትር መሰናክል 7:52.11 በሆነ ጊዜ በመግባት የዓለም ሪከርድን መስበሩ ይታወሳል፡፡ ሁለቱ ጠንካራ አትሌቶች እርስ በርስ ሲገናኙ የዛሬ ምሽቱ በሩጫ ህይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ኢንጌብሪግስቴን ለምሽቱ ፍልሚያ 100 ፐርሰንት መዘጋጀቱን ገልፆ ለማሸነፍ እና ከተቻለውም ላለፉት 25 ዓመታት የሚደፍረው ያጣውን የሞሮኳዊውን ሂሻም ኤልጉሩዥ ሪከርድ (3፡26.00) ለመስበር እንደሚጥር አስታውቋል፡፡

ታደሰ ለሚም ሌላኛው በውድድሩ የሚሳተፍ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዚህ መድረክ አንድም ኬንያዊ እና ኡጋንዳዊ አትሌቶች የሉም፡፡

በ5000 ሜትር ወንዶች 16 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሰባቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

ይሄም ለአሸናፊነቱ ከፍተኛ ግምትን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ጥላሁን ሃይሌ፣ ገመቹ ዲዳ፣ ቦኪ ድሪባ፣ ሙክታር እንድሪስ እና ኩማ ግርማ ተሳታፊዎቻችን ናቸው፡፡

በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነው ብርሃኑ ባለው፣ ብሩንዲያዊው ኤጂድ ንታካሩቲማና እና ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጊ የአትሌቶቻችን ተፎካካሪዎች ሆነው ያመሻሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል በዓለም ከ20 ዓመት በታች የብር ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችውና በቅርቡ ጣልያን ፍሎሬንስ ላይ 9፡00.71 በመሮጥ በርቀቱ የዓመቱን እና የራሷን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበችው ሲምቦ አለማየሁ ከሀገሯ ልጆች መቅደስ አበበ፣ ሎሚ ሙለታ እና ዘርፌ ወንድማገኝ ጋር ትፎካከራለች፡፡

በርቀቱ የዓለም ሪከርድ (8:44.32) ባለቤት የሆነችውና በርቀቱ ከ8፡50 እና 45 በታች በመግባት በታሪክ የመጀመሪያዋ አትሌት የሆነችው ኬንያዊቷ ቢትሪስ ቼፕኮኤች እና የሀገሯ ልጅ ፋንሲ ቼሬኖም ከአትሌቶቻችን ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡

በ800 ሜትር ሀብታም አለሙ ብቸኛ ተወዳዳሪያችን ናት፡፡

ኬንያዊቷን ማሪ ሞራን ጨምሮ ከታላቋ ብሪታኒያ፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ፖላንድ፣ ጃማይካ እና ቤኒን አትሌቶች ጋር ብርቱ ፉክክር እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡

በምስጋናው ታደሰ
ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *