የቅዱስ ቁራን መቃጠልና የስዊድን ኔቶን የመቀላቀል ጉዞ ፈተና

በስዊድን ቅዱስ ቁርአን መቃጠሉን ተከትሎ ሀገሪቱ ኔቶን እንዳትቀላቀል ያደርጋታል ተባለ፡፡

በስቶኮልም የሆነዉ ሀገሪቱን ከአረቡ አለም ብቻም ሳይሆን ያጋጫት ወደ ኔቶ ለመግባት የምታደርገዉን ጉዞ እንዳያጨልምባት ተሰግቷል፡፡

በኖርዲኳ ሀገር የሆነዉ ሁሉ የዕምነቱ ተከታዮችን በእጅጉን አስቆጥቷል፡፡
ስቶኮልምን ሙስሊም ጠል አክራሪዎች ዋጋ እንዳያስፈልጓት ተሰግቷል፡፡
የአረቡ አለም ሁሉ በስዊድን ስቶኮልም በሆነዉ ነገር ቁጣዉን እየገለፀ ይገኛል፡፡

የድርጊቱ መደጋጋም ደግሞ በተለይም እነ አንካራን በእጅጉ ነዉ ያሳዘነዉም ያስቆጣዉም፡፡

ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶን ለመቀላቃል ያላት ሄልም እዉን የሚሆነዉ በተርኪዬ በጎ ፍቃደኝነት ነዉ፡፡

ምክንያቱም ቁልፉ በፕሬዝዳንት ረሲጵ ጣይፕ ኤርዶሃን እጅ ላይ ይገኛልና፡፡

አንድ ግለሰብም የቅዱስ ቁርአን ገጾችን በመቦጫጨቅ በእሳት ሲያያዝ ሌሎቹ አቃጥለው እያሉ የድጋፍ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር።

በስዊድን ጸረ እስልምና ይዘት ያላቸው ተቃውሞዎች ሲደረጉ ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም በአረፋ እለት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በተሰባሰቡበት መስጂድ ዙሪያ ቁርአን በማቃጠል የተገለጸው ተዋውሞ በርካቶችን አስቆጥቷል።

በስዊድን በርካታ የኢራንና የኢራቅ ስደተኞች ይኖራሉ፡፡

ይህን ሙስሊምና ስደተኛ ጠል የሆነውን ቡድን የሚመራው የዴንማርክና ስዊድን ጥምር ዜግነት ያለው ራስመስ ፓሉዳን የሚባል ግለሰብ ነው፡፡

የቡድኑ ስም ስትራም ኩርስ ይባላል፡፡ራስመስ የቀኝ አክራሪ ሲሆን ጥቁሮች፣ ሙስሊሞችና በአጠቃላይ ስደተኞች ከአካባቢው አገራት ጠቅልለው እንዲወጡ የሚታገል ነው፡፡

ራስመስ ፓሉዳን በስካንዲኒቪያን የቀኝ አክራሪዎች ዘንድ ስሙ የገነነ ሰው ሲኾን ሙስሊምና ጥቁር ጠል በመሆኑ ይታወቃል፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስቴርሰን በሰጡት መግለጫም፥ ቁርአን የማቃጠሉን ጉዳይ ተገቢ አይደለም ግን ህጋዊ ነው በሚል አልፈውታል።

የስቶኮልም መስጂድ ኢማም ሞሃመድ ካሊፋ ግን ፖሊስ በኢድ አል አድሃ በዓል በመስጂዱ ዙሪያ የተቃውሞ ስልፍ እንዲደረግ መፍቀዱን አጥብቀው ተቃውመዋል።

ስቶኮልም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶን የመቀላቀል ሂደትም በአንካራ ይሁንታ ላይ እንደመመስረቱ መጓተቱ እንደማይቀር ተገልጿል።

ከዚህ በፊት በስቶኮልም በሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ቁርአን መቃጠሉን ተከትሎ ቱርክ ከስዊድን ጋር በኔቶ ጉዳይ መነጋገር ማቆሟ ይታወሳል።

የተርኪየዉ ፕሬዝዳንት ረሲጵ ታይፕ ኤርዶዋን ስዊድን ከኩርድ ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸውን በርካታ ሰዎች አሳልፋ አልሰጠችም ሲሉ በተደጋጋሚ ይከሳሉ።

ኔቶን መቀላቀል ከፈለጋችሁ፤ እነዚህን አሸባሪዎች ታስረክቡናላችሁ ሚል አቋም አላቸዉ ፕሬዝዳንቱ።

ስዊድን ከፊንላንድ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኩርድ ዳያስፖራ አባላት አላት።

ቱርክ አሸባሪ ብላ ከሰየመችው የኩርዲስታን ሠራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ስዊድን እራሷን እንድታርቅ በተደጋጋሚ ስታጠነቅቅ ቆይታለች።

ሁለቱ የኖርዲክ አገራት ከቱርክ ጋር ያላቸው ግንኙነት መሻከር ከጀመረ ሰነባብቷል።

ቱርክ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት መሳተፍ መጀመሯን ተከትሎ ስዊድን እና ፊንላንድ ለቱርክ የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዳይደርግ እገዳ ጥለዋል።

በዚህም ምክንያት ነዉ አንካራ የስዊድንን ወደ ሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የመቀላቀሏ ህልም እዉን እንዳይሆን አስራ ያስቀመጣች፡፡

የአሁኑ ድርጊት ደግሞ አንካራን ከማስቆጣቱ ባለፈ እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲሉ የአንካራና የስቶኮልምን ዉጥረት እንዳያባብሰዉ ተሰግቷል ይላል የአልጄዚራ ዘገባ፡፡

ከስዊድኑ ድርጊት በኋላ በርካታ የአረብ ሀገራት እና አሜሪካ የተቃዉሞ መግለጫ አዉጥተዋል፡፡

የነጩ ቤተመንግስት ሰዎች ግን ተርኪዬ ቶሎ ብላ ስዊድን ወደ ሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ እንድተቃለቃል ትፍቀድላት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ኢራን ፤ ሳዉድ አረቢያ፤ ግብፅ የመን፤ ኩዌይት፤ ኢራቅ፤ ጆርዳን፤ ሶሪያና ፍልስጤም የስዊድኑን ድርጊተቀባይነት የሌለዉና እጅግ አደገኛ ቀዉስ ሊያስከትል የሚችል የሽብር ተግባር ሲሉ ክፉኛ ወቅሰዋል፡፡

አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ በበኩሏ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጣት በሀገሯ የሚገኙትን የስዊድን አምባሳደር በአስቸኳይ እንደጠራች አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

ይህም ስዊድን ከአረቡ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኑነት እንዳያበላሽባት ከመሰጋቱም በላይ ኔቶን የመቀላቀል ህልሟ እንዳይጨልምባት ከፍ ሲልም ከአንካራ ጋር እንዳያላትማት ስጋትን ደቅኗል፡፡

በአባቱ መረቀ
ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.