በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር የ87 ሰዎች አስከሬን ተቀብሮ መገኘቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታዉቋል፡፡
በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ እና በተባባሪ ሚሊሻዎቻቸዉ የተገደሉ 87 ሰዎች አስከሬን ከከተማዋ መዲና ኢል-ጀኒና አቅራቢያ መገኘታቸዉን ገልጿል፡፡
ታማኝ ምንጮቼ ነግረዉኛል ያለዉ ድርጅቱ በፈጥኖ ደራሹ ሃይል ትዕዛዝ ሰጪነት መገደላቸዉን አረጋግጫለዉ ነዉ ያለዉ፡፡
የአከባቢዉ ነዋሪዎች አስከሬኖቹን እንዲቀብሩ መገደዳቸዉን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የገለጹ ሲሆን በሰኔ 20፣ 37 አስከሬኖችን አንድ ሜትር ጥልቀት ባለዉ ጉድጓድ ዉስጥ መቅበራቸዉን ተናግረዋል፡፡
በነጋታዉ ሰኔ 21 ደግሞ የ 50 ሰዎችን አስከሬን እዛዉ ቦታ ላይ መቅበራቸዉን ገልጸዉ የ 7 ሴቶች እና የ 7 ህጻናት አስከሬንም መኖሩን አስታዉቀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከታማኝ ምንጮቼ አገኘሁት ባለዉ መረጃ መሰረት እነዚህ ሰዎች ከሰኔ 13-21 ባለዉ ጊዜ ዉስጥ በፈጥኖ ደራሹ ሃይል እና በተባባሪ የሚሊሻ ደጋፊዎቹ መገደላቸዉን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ከሟቾቹ መካከል የምዕራብ ዳርፉር ገዢ የነበሩት ግለሰብ ካሃሚስ አባበከር የሚገኙበት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በጥይት ተመተዉ ህክምና ማግኘት ያልቻሉ ሰዎችም ተቀብረዉ መገኘታቸዉ ተገልጿል፡፡
በእስከዳር ግርማ
ሐምሌ 06 ቀን 2015 ዓ.ም











