ባሳለፍነው ረቡዕ ትብብር የፈጠሩት አምስትስ ፓርቲዎች መግለጫ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በሀገራችን የተለያዩ ዘመናት የነበሩ አሁንም ድረስ ያሉ መንግስታት ተቃሚዎችን የማጥፋት እና ህዝብ አማራጭ እንዳይኖረው ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የሀገራችን ችግር ተቋማዊ እና ህገመንገስታዊ በመሆኑ ተቋማት ሳይኖሩ ምንም መፍጠር አይቻልም ያሉት አቶ የሺዋስ፣ መንግስት በሀገሪቱ አማራጭ እንዲኖርና ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ፓርቲዎች በሀገር ላይ ትልቅ ድረሻ እንዳላቸው መንግስት መገንዘብ አለበት ያሉ ሲሆን በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሀገር ጉዳይ ላይ ሀሳብ ይሰጣሉ እንዲሁም ይታገላሉ ብለዋል፡፡
በሀገር ለውጥ መምጣት የሚችለው ዲሞክራሲም ሊረጋገጥ የሚችለው በሀሳብ ፍጭት ብቻ ነው ያሉት አቶ የሺዋስ ኢትዮጵያ በዚህ ሰዓት አደጋ ውስጥ እንደመገኘቷ ፓርቲዎች በጋራ ሰብሰብ ብለው መታገል ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጠንካራ መሪዎች እንጂ ጠንካራ ተቋማት ኖሯት አያውቅም ይህ ደግሞ መንግስታት ሲያጠፉ በቃ የሚል ተቋም መገንባት አለብን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ባሳለፍነው ረቡዕ ኢህአፓ፣መኢአድ፣እናት፣የአማራ ግዮናዊት ንቅናቄ እና አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ትብብር መፍጠራቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
በአቤል ደጀኔ
ሐምሌ 07 ቀን 2015 ዓ.ም











