መተግበሪያው ከ”ትረስትድ ቴክ ትሬዲንግ ፒ ኤል ሲ” ጋር በመተባበር የበለጸገ ሲሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሞባይሉን ወይም ላፕቶፑን በመጠቀም ባመቸው ሰዓትና ቦታ የፈለገውን ያህል የእርዳታ ገንዘብ ለመለገስ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም ፕላትፎርሙ በሃገራችን በተለያዩ ማህበራዊ የአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለሚነድፏቸው ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡
ይህ ፕላትፎርም/መተግበሪያ በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሰራበት ከሚገኘው “Go fund me platform” ጋር በአይነቱም በአስተማማኝነቱም ተመሳሳይ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ተከስተ መተግበሪያው ትግራይን ጨምሮ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት በሚደረገው ጥረት የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ተሳትፎ ለማጎልበት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ ተቋማትን ( ትምህርት ቤት፣ጤና ጣቢያዎች፣ሆስፒታሎች…) እና ሌሎችንም ተቋማት መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከዲያስፖራው ገንዘብ ለማሰባሰብ እቅድና ፍላጎቱ ያላቸው ድርጅቶች ባንኩ ያዘጋጀውን አንበሳ ፈንድ ተጠቅመው ማሰባሰብ እንዲችሉ ባንኩ እድሉን እንደሚያመቻችም ገልጸዋል፡፡
አቶ ዳንኤል አክለውም አንበሳ ፈንድ የእርዳታ ማሰባሰቢያ መተግበሪያ ድረ-ገጽን መሰረት አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ትውልደ-ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሞባይል ስልኮቻቸውም ሆነ በሌሎች የትስሰር ገጾቻቸው አማካይነት ወደ አንበሳ ፈንድ ድረ-ገጽ www.anbesafund.com በቀላሉ ገብተው የፈለጉትን ያህል የገንዘብ ልገሳ በማድረግ በሀገራቸው ልማት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን እንደሚያስችላቸው ጠቅመው፣ ይህን እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
መተግበሪያው የተለያዩ የፍተሻ ደረጃዎችን አልፎ ወደ ትግበራ የገባ ሲሆን ከእርዳታ ማሰባሰቢያነት ባሻገር አክሲዮን ለመሸጥ የሚፈልጉ ድርጅቶችም ይህንኑ መተግበሪያ በመተቀም መሸጥ እንደሚችሉም የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ተከስተ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ 07 ቀን 2015 ዓ.ም











