በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የቡድኑ ታጣቂዎች በወረዳው የገጠር ቀበሌዎች በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ሰምተናል።
የወረዳው ነዋሪዎች ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት ታጣቂዎቹ ከሰሞኑ በስፋት መንቀሳቀስ በመጀመራቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ወደ ወረዳው የገጠር ቀበሌዎች እየገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ታጣቂዎቹ ከዚህ ቀደም በወረዳው በተደጋጋሚ ባደረሱት ጥቃት በርካታ ዜጎች መገደላቸውንም ነዋሪዎቹ አስታውሰዋል።
በተጨማሪም በወረዳው የገጠር ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ታጣቂዎችን ሸሽት ወደ ወረዳዋ ከተማ ጉንዶ መስቀልና ወደሌሎች አካባቢዎች መሰደዳቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የሽብር ቡድኑ ታጣቂውች በወረዳው የገጠር ቀበሌ በሆኑ ባቡ ድሬ፣ ራቾና ድሬ መንቃታ አካባቢዎች በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ነው የተነገረው።
ኦነግ ሸኔ ከ ሁለት አመት በፊት ጀምሮ ወደ ወረዳው በመግባት ዜጎችን በማገት ገንዘብ መቀበል እንዲሁም ግድያና ማፈናቀል እያደረሰ ነው ተብሏል።
በተለይም የደራ ወረዳን ከሰላሌ ጋር የሚያገናኘውን የጀማን ድልድይ በመቆጣጠሩ የወረዳዋ ነዋሪዎች በአማራ ክልል መርሐቤቴ ወረዳ በኩል ወደ አዲስ አበባ እንዲሚመጡ ተገደዋል።
የደራ ወረዳ ከአዲስ አበባ 2 መቶ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ወረዳ መሆኑ ይታወቃል።
እኛም ወቅታዊውን የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በተመለከተ የወረዳውን አስተዳዳሪ ለማናገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም።
በአባቱ መረቀ
ነሃሴ 08 ቀን 2015 ዓ.ም











