ከዚህ ቀደም ከ300 በላይ በሙያዉ ላይ ባሉ አካላት “ሙያዬ ለሀገሬ የበጎነት ማህበር” ተብሎ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ባለሙያዎች በጋራ በመሆን፣ የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበርን መመስረታቸዉን በዛሬዉ ዕለት አስታውቀዋል።
በዛሬዉ ዕለት ምስረታዉን ያደረገዉ የማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ፣ በሆቴል ቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አስታዋፅኦ ለማድረግ ታስቦ የተመሠረተ መሆኑን ተናግረዋል።
ማህበሩ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በኮቪድና በተለያዩ ችግሮች የተጎዳዉን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ታስቦ በ228 አባላት የተመሠረተ ሲሆን የአባላቱ ቁጥር ከዚህም ሊጨምር እንደሚችልም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር በሲቪል ድርጅቶች ባለስልጣን የተመዘገበ ማህበር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሰፊ ልምድና ብቃት ባላቸዉ ባለሙያዎች አጋርነት መመስረቱ ነው የተገለጸው፡፡
ልህቀት፣ ተባባሪነት መገለጫችን ነዉ የሚለዉ ማህበሩ፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከሀገሪቱ አምስት ዋና የኢኮኖሚ ምሶሶዎች አንዱ ከመሆኑ አኳያ የፖሊሲ ግብዓት ለሚመለከተዉ የመንግስት አካል ያቀርባል ተብሏል።
በማህበሩ ምስረታ መርሀ-ግብር ላይ የአዲስ አበባ ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳዉ፣ ይህን መሰል ማህበር መመስረቱ በሃገሪያ ያሉ ቱርዝም ጸጋዎችን በሚገባ ለማስተዋወቅና ከዘርፉ ሚገባትን ገቢ እንድታገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም











