የሳልሳይ ወያኔ ትግራይን ሁለት የፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ፍረድ ቤት በዋስ ቢለቃቸውም ፖሊስ ይህንን ተፈፃሚ አለማድረጉን የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ የፖለቲካ ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ ክንፈ ሀዱሽ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ሊካሄድ ታስቦ በነበረው በጷግሜ ሁለቱ ሰለማዊ ሰልፋ ጋር በተያያዘ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋዜጠኞች እንዲሁም አክቲቪስቶች በትግራይ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም በርካቶቹ መፈታታቸው ተገልፃል፡፡
በሰልፉ ወቅት በነበረ ወከባ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሷባቸው ለእስር ተደርገዋል የሚሉት አቶ ክንፈ ታስረው የነበሩት በርካቶች እየተፈቱ ቢሆንም የአራት ድርጅት አመራሮች አሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የውናት ሊቀመንበር ዶ/ር ደጀን መዝገበ ፣የሳወት ሊቀመንበር ሃያሉ ጎዱፋይ ፣የዓረና ሉአላውነትና ዴሞክራሲ ሊቀመንበር ዓንዶም ገ/ስላሴ ፣የባይቶና ዓባይ ትግራይ አስተባባሪ ኪዳነ ኣመነ ፣የባይቶና ዓባይ ትግራይ አስተባባሪ ክብሮም በርሀ ፣የሳወት ከፍተኛ አመራር ዓብለሎም ገ/ሚካኤልና አሁንም ድረስ በእስር እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡
ጷግሜ ሁለቱ ተጠርቶ የነበረው ሰልፍ ዓላማ በትግራይ ክልል ያለውን ከፍተኛ የሆነ ችግር በተመለከተ ግዚያዊ አስተዳደሩ ላይ ጫና ለማሳደር ታስቦ የነበረ መሆኑን ለጣብያችን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የትግራይን ሉዓላዊነት ከማስከበር አኳያ፣ከተፈናቃዮችና ርሃብ ጋር በተያያዘ ያለውን መጠነ ሰፊ ችግር ፣የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ እንዲከፈላቸው እንዲሁም የፀጥታ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ጫና ለማድረግ ያተሰበ ነበር ተብሏል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ጳጉሜ 06 ቀን 2015 ዓ.ም











