ከወሰን ጋር በተያያዘ አለመግባባት የተፈጠረባት የወልቂጤ ከተማ፣ የወሰን ማስከበር ስራው በአስቸኳይ እንዲሰራ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተደራጀ በኃላ ከወልቂጤ ከተማ ወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ከአዋሳኝ አካባቢዎች አለመግባባት መፈጠሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

አዲሱ “የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል” በተመሰረተበት ጉባኤ አዳዲስ መዋቅሮች እራሳቸውን ችለው እንዲደራጁ መፅደቁ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት ወልቂጤ ከተማ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አካል ሲሆን፣ የወልቂጤ ከተማ አዋሳኝ የሆነው የቀቤና ወረዳ በልዩ ወረዳነት እንዲደራጅ ተወስኗል።

እስካሁን ባለው ሂደት አዲሱ ልዩ ወረዳ አዲስ መቀመጫ ይሰይማል፣ ወይስ ወልቂጤ ይቆያል? የሚለው የታወቀ ነገር የለም ሲሉ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ልዩ ወረዳው ወልቂጤ የሚቆይ ከሆነ ከከተማዋ አስተዳደር ጋር የሚኖረው ግንኙነት ምን ይሆናል? የሚለው ከወዲሁ በግልጽ መታወቅ አለባቸው ነው የሚሉት፡፡

ወልቂጤ ከተማ በህግ የፀደቀ የከተማ ፕላን ቢኖራትም፣ በፀደቀው ፕላን መሰረት የከተማዋን ወሰን የሚያስከብር አካል ባለመኖሩ፣ ከተማዋ ለበርካታ ችግሮች እንድትጋለጥ አድርጓታል ሲሉም አስተያየት ሰጭዎቹ ያነሳሉ፡፡

የከተማዋ የወሰን ማስከበር ስራ በአስቸኳይ ካልተጠናቀቀ፣ የከተማዋን ልማት እና ሰላም ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ሊያወሳስበው እንደሚችል የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የዞኑ እና የከተማዋ አመራች የከተማዋን ሰላም እና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የከተማዋን የወሰን ማስከበር ስራ እንዲሰሩ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

መስከረም 07 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.