ኢትዮጵያ ከ30 በመቶ በላይ የግብርና ምርቷን በድህረ የምርት አሰባሰብ ወቅት እንደሚባክንባት አንድ ጥናት አመለከተ።

በዚህም ምክንያት ከ 100 ሚሊየን በላይ እንደሆነ ከሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል 25 ሚሊየኑ በቂ ምግብ እንደማያገኝ ጥናቱ አመላክቷል።

ይህም እየሆነ ያለው በምርት እጥረት ሳይሆን ፣በድህረ ምርት ወቅት በሚፈጠር ብክነት መሆኑን በአዲስአበባ ዩንቨርስቲ የምግብ እና የስነምግብ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አሻግሬ ዘውዱ ተናግረዋል።

ብክነቱ የሚጀምረው ከግብርናው አንስቶ ቤታችን እስኪደር ባለው ሂደት ነው የሚሉት የስነምግብ ባለሞያው በግብርና ቦታ 14 በመቶ እና በቤታችን ደግሞ 17 በመቶ እንደሚባክን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የድህረ ምርት ብክነት ማህበር ባጠናው አዲስ ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ ከሚመረተው የግብርና ምርት ከ10 እስከ 30 በመቶ ይባክናል ሲሉ የማህበሩ አባል ዶክተር አሻግሬ ተናግረዋል።

በእህል ምርቶች እስከ 30 በቶ ፤በአትክልት ምርት እስከ 60 በመቶ በፍራፍሬ ምርቶች ደግሞ እስከ 70 በመቶ በሚፈጠር ብክነት ሰዎች ለምግብ እጦት ይዳረጋሉ ብለዋል።

በክልል የተመረቱ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል ወይም ከልሎች አካባቢዎች ወደ መዲናዋ እስኪደርሱ ድረስ እስከ 50 በመቶ እንደሚባክኑ ገልጸዋል።

እየባከነ የሚገኘው የግብርና ምርትም የኢትዮጵያን 25 ሚሊየን የሚሆነው ህዝብ መመገብ የሚችል መሆኑን ጥናቱ እንደሚያመላክት ዶክተር አሻግሬ ዘውዱ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የግብርና ምርቶችን ለመሰብሰብ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን አለመጠቀም ፤የሎጅስቲክስ ችግር እና በሃገሪቱ የሚስተዋለው የሰላም እጦት ዋና ምክንያቶች ናቸው ተብሏል።

በመሳይ ገ/መድህን
መስከረም 09 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.