100 ኪሎ ጤፍ—-15 ሺህ ብር፤

በአዲስ አበባ 100 ኪሎ ጤፍ 15 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል፡፡

አንደኛ ደረጃ ማኛ በመባል የሚታወቀው ጤፍ ወፍጮ ቤቶች ላይ 15ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ኢትዮ ኤፍ ኤም ባደረገው ቅኝት ለመታዘብ ችሏል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ ወፍጮ ቤቶች በተሰናበትነው 2015 ዓ.ም 100 ኪሎ ጤፍ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ ሲሸጥ ነበር፡፡

አሁን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የ4ሺህ ብር እና የ5ሺህ ብር ጭማሪ አሳይቶ እስከ 15 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም በተለያዩ ወፍጮ ቤቶች ያለዉን የጤፍ ዋጋ በአካል በመገኘት ለማጣራት ሞክሯል።

በዚህም መሰረት ነጭ ጤፍ (ማኛ) በኪሎ ከ140 እስከ 150 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ታዝበናል፡፡

እንደዚሁም ሰርገኛ እና ነጭ 100 ኪሎ ጤፍ ደግሞ እስከ 13 ሺህ ብር ይሸጣል፡፡

የጤፍ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች፣ ነጋዴዎች እና የወፍጮ ቤት ባለቤቶችም ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

የነዋሪዎችን አቅም ከተፈታተነው የዋጋ ጭማሪ ባሻገር፣ በገበያው በቂ የሚባል የጤፍ አቅርቦትም የለም ሲሉ የወፍጮ ቤት ባለንብረቶች ነግረውናል፡፡

አስተያየት ሰጭዎች እንዳሉት በሸማች ማህበራት 100ኪሎ ጤፍ በ10ሺህ ብር ድረስ ይሸጣል ያሉ ሲሆን የጤፉን አይነትና ደረጃ ግን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ በጤፍ ዋጋ ላይ የታየው ጭማሪ መሰረታዊ ምክንያቱ ምን ይሆን?

ለዚህ ጥያቄ ነጋዴዎች እና ወፍጮ ቤቶች ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
ነጋዴዎች ጤፍ ጠፍቶ ሳይሆን ወደ ገበያ አለመቅረቡ ነው ይላሉ፡፡
ለዚህ ደግሞ በሃገሪቱ የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ነው የተናሩት፡፡

ከፍተኛ መጠን ያለው የጤፍ ምርት የሚቀርበው ከጎጃም ነበር የሚሉት ነጋዴዎች፣ አሁን በክልሉ ባለው አለመረጋጋት የጤፍ ምርት ወደ ገበያ እየቀረበ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የወፍጮ ቤት ባለቤቶችንም ጠይቋቸው ነበር፡፡

ወፍጮ ቤቶች ጤፍ በበቂ እንደማያገኙ ተናግረው ፍላጎቱ ከወትሮው የተለየ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት 50 ኩንታል እና ከዛ በላይ ይቀርብልን የነበረው ጤፍ አሁን በግማሽ ቀንሶብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጤፍ ያስረክቡን የነበሩ ነጋዴዎችም ሌላ ደንበኞችን መያዝ ጀምረዋል ያሉት ነጋዴዎቹ፣ ሌሎች ደንበኞች የሚሏቸው ሆቴል ቤቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በጤፍ ገበያ ላይ እጃቸውን ያስገቡ ደላሎች በቀጥታ ጤፍ ሸማቹ እጅ ላይ እንዳይገባ እየሰሩ ናቸው፤ ከሆቴል ቤቶች ጋር በመመሳጠር የዋጋ ንረት እንዲፈጠር እያደረጉ ናቸው ሲሉ ትዝብታችን ነግረውናል፡፡

ሰዎች ነገ ይበልጥ ይጨምራል በሚል ብዙ ለመግዛት የሚያደርጉት ግብግብ ዋጋው ይበልጥ እንዲጨምር አድርጎታል፤በቂ አቅርቦት ቢኖር ግን ይህ አይፈጠርም ነበር ብለዋል የወፍጮ ቤት ባለንብረቶች፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.