በአስራኤና በሃማስ መካከል በተቀሰቀሰዉ ጦርነት በሀገሪቱ የሚገኙ ቤተ እስራኤላዉያንና ኢትዮጵያውያን የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸዉ ተሰማ፡፡

ሃማስ በእስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በሀገሪቱ የሚገኙ ቤተ እስራኤላዉያንና ኢትዮጵያዉያን የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸዉን በኢትዮጵያ እስራኤል ኤምባሲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታዉቋል፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለሊ አደማሱ በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ዙሪያ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤የጉዳቱን መጠን አሁን ላይ መግለጽ ባይቻልም ከተጎጂዎች መካከል ግን ቤተ እስራኤላዉያንና ኢትዮጵያዉያን እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

በጥቃቱ ከ7 መቶ በላይ እስራኤላዉያን መሞታቸዉን አምባሳደር አለሊ አስታዉቀዋል፡፡

በተጨማሪም ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዉ በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ የእስራኤል ጦር ኃይል የሃማስን ጥቃት በመመከት ጎን ለጎን የሞቱ ዜጎችን እየቀበረ እንደሚገኝ ኤምባሲዉ አስታዉቋል፡፡

ሃማስ የጀመረዉ ጥቃት በቀላሉ የሚታልፍ እንዳልሆነም አምባሳደር አለሊ ገልጸዋል፡፡

እስራኤል አንድ መቶ ሺህ ወታደሮቿን ወደ ጋዛ ማሰመራቷንም አስታዉቃለች፡፡

የሀገሪቱ መከላከያ ሃይልም ከዚህ ጦርነት በኋላ ሃማስ የሚባል የታጠቀ ሃይል እስከመጨረሻዉ ያሸልባል፤ ከምድረ ገፅም ይጠፋል እያለ ነዉ፡፡
የእስረኤል ጦር ከሃማስ ወታደሮች ጋር በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል እልህ አስጨራሽ ጦርነት እያካሄዱ መሆኑ እየተነገረ ነዉ፡፡

በአሁኑ ሰኣት ጦርነቱ በተለይም ኪቡዝ ካርሚያ እንዲሁም አሽኬሎንና ሲድሮት በተሰኙ ከተሞች ሁኔታዉ አስከፊ መሆኑን የአለም አቀፍ መገኛኛ ብዙሃን የእስራኤልን የጦር ሓይል ጠቅሰዉ በቀጥታ እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ጦርነት የእስራኤል የጦር አመራሮች ጭምር ሳይጎዱ እንዳልቀሩ የአልጄዚራዉ ሙሃመድ ጃምጁም ከምእራብ እየሩሳሌም ዘግቧል፡፡
የጦር ሃይሉ ቃል አቀባይ ዮናታን ኮንሪከስ በአሁኑ ሰኣት አንድ መቶ ሺህ ተጠባባቂ ወታደሮችን በደቡባዊ እስራኤል በኩል ወደ ጋዛ እያስጠጋን ነዉ ብለዋል፡፡

‘‘አሁን ስራችን ሁሉ ይሕን ጦርነት በበላይነት ማጠናቀቅ ነዉ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋም ሃማስ የሚሰኘዉ ቡድን እስከመጨረሻዉ ይሸኛል ከዚያ በኋላም ለእስራኤል ስጋት መሆኑ ያካትማል‘‘ ነዉ የተባለዉ፡፡

በዚህ ጦርነት ምክንያት ከሁለቱም ወገኖች አንድሺ የሚጠጉ ዜጎች መገደላቸዉ ተነግሯል፡፡

በጋዛ ምድር ደግሞ 1 መቶ 23 ሺህ 5 መቶ38 ዜጎች መፈናቀላቸዉ ተሰምቷል፡፡አንድ መቶ እስራኤላዉያን ደግሞ በሃማስ ታፍነዋል፡፡
የእስራኤል ባለሥልጣናትም ከዚህ በፊት ካጋጠሙት በእጅጉ የተለየ ስለሆነው የሐማስ ጥቃት ሲጠየቁ “እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ ምንም አናውቅም” የሚል ነው ምላሻቸው።

በመካከለኛው መሥራቅ ካሉ አገራት ሁሉ አስራኤል ከፍተኛ ሃብት የሚፈስበት መጠነ ሰፊ ተጽእኖ ያለው የመረጃ እና ደኅንነት አላት።

የደኅንነት ተቋሞቿ በሌባኖስ፣ በሶሪያ እና ሌሎች አገራትን ጨምሮ በፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ውስጥ ሳይቀር መረጃ አቀባዮች አሏቸው።

በዚህም የታጣቂ ቡድኖችን መሪዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴን በትክክል ከመከታተል በተጨማሪ አስፈላጊ ሲሆን በማያወላዳ ሁኔታ ግድያን አስከመፈጸም የሚደርስ እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል።

እስራኤል ሃማስን እስከወዳኛዉ ሳላፀዳ ጦርነቱን አላቆምም እያለች ትገኛለች፡፡

ብሪታንያ፤ ፈረንሳይና ጀርመንን የመሳሰሉ ሀገራትም በሀገራቸዉ የሚገኙ አይሁዶች ላይ ጥቃት ይደርሳል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡
የሊባኖሱ ሄዝቦላም ከሃማስ ጎን መሰለፉን በግልጽ አስታዉቋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የእስራኤል አየር ሃይል በሊባኖስና በሶሪያ ድንበር አካባቢ በሄዝቦላህ የጦር መንደሮች ላይ ጥቃት ከፈቷል፡፡

ይህ ደግሞ ቀጠናዉን ወደ አስከፊ ሁኔታ እንዳያስገባዉ ተሰግቷል፡፡
ከሃማስና ከሄዝቦላህ ጀርባ ኢራን አለች ስትል እስራኤል እየከሰሰች ነዉ፡፡
ኢራን በበኩሏ በርግጥ አሁንም ቢሆን ከፍልስጤማወያን ጎን ነኝ፤ ነገር ግን በአሁኑ የሃማስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ስትል ባወጣችዉ መግለጫ አስታዉቃለች፡፡

አሜሪካ ደግሞ ለእስራአል አጋርነቷን ለማሳየት የጦር መርከቦቿንና ጄቶቿን ወደ ስፍራዉ እያሰጠጋች መሆኗን የመከላከያ ሚኒስትሩ ሊዮድ ኦስቲን አስታዉቀዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸፅታ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ተሰብስቦ ሳይስማማ ተበትኗል፡፡

በጉዳዩ ላይ አዲስ አበባ የሚገኘዉን የፍልስጤም ኤምባሲ ለማነጋገር ያደረግነዉ ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

በአባቱ መረቀ

መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.