በትግራይ ክልል ከ14 ሺህ በላይ መምህራን ከስራ ገበታ ውጭ ናቸው ተባለ።

በ2012 ከነበሩት 46 ሺህ በላይ መምህራን አሁን ላይ ከ14ሺህ በላይ የሚሆኑት ከስራ ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል።

የትምህርት ቢሮው ሀላፊ ዶ/ር ኪሮስ ግዑሽ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የሰሜኑ ጦርነት የብዙ መምህራንን ህይወት አመሰቃቅሏል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት የተሰደዱ ፣ የተፈናቀሉ ፣ አካላቸው የጎደለ እንዲሁም የሞቱ መምህራን መኖራቸውን አንስተው፤ ከ 2 ዓመት በላይ ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ህይወታቸውን ለማትረፍ የተለያዩ ስራዎች ውስጥ የተሰማሩ መኖራቸውንም ገልፀዋል።

የተቀሩት መምህራንም ቢሆኑ በጦርነቱ ምክንያት ብዙ የስነልቦና ጉዳትን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ችግር ደርሶባቸዋል ነው ያሉን።

በክልሉ የነበረው ጦርነት በትምህርት ዙሪያ ሶስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷልም ነው ያሉት ሃላፊው።

የት/ቤቶች መቃጠል ፣መፍረስ፣ መውደም አንደኛው ሲሆን ፤ በሰው ሃይሉ ላይ ያደረሰው ጉዳት ቀጥሎ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

በሶስተኛነት የተነሳው ጉዳይ ደግሞ ስርዓተ ትምህርቱ ሲሆን ብዙ ተማሪዎች በእድሜያቸው ልክ ማግኘት ያለባቸውን ትምህርት ባለማግኘታቸው አሁን ላይ 5ኛ ክፍል እና ከዛ በላይ መሆን የነበረባቸው ልጆች ገና የ1ኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በ2012 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ቢወስዱ ምናልባት አሁን ላይ የ4ኛ አመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሚሆኑ ከ9ሺህ በላይ ተማሪዎች ከ4 አመታት በኋላ ባለፈው ሳምንት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መውሰዳቸው የሚታወስ ነው።

በእስከዳር ግርማ

ጥቅምት 06 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.