በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር ምርቶች ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውረው እንዳይሸጡ እያደረገበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ገልጿል፡፡

ባለፉት አመታት በኢትዮጰያ የተለያዩ አከባቢዎች እየተደረጉ የነበሩ እና አሁንም በመደረግ ላይ የሚገኙ ግጭቶች፣ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎችን እያዳከማቸው እንደሚገኝ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙልጌታ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ምርቶችን ከመሸጥ ባለፈ ኢንዱስትሪዎች የብረታ ብረት ምርት ግብዓቶችን የሚሰበስቡት ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በመሆኑ የጸጥታው ሁኔታ ይህንን እንዳስቀረው አንስተዋል፡፡

ከዚህም የተነሳ የብረታ ብረት ገበያው በከፍተኛ ደረጃ መቀዛቀዙን እና በዘርፉ ላይ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እጅጉን መዳከሙን ስራ ስኪያጁ ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡

የህገ-ወጥ ንግዱ ከሰላም ማጣቱ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ያነሱት አቶ ሰለሞን፣ መንግስት በሰላሙ ላይ ትኩረት በማድረጉ ህገ-ወጥ አካላት ይህንን አጋጣሚ እየተጠቀሙ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዘርፉን ክፉኛ እየፈተነው እንደሚገኝ ስራ አስኪያጁ ገልጸለዋል፡፡

ከዚህም የተነሳ ገበያቸውን ማሳደግ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች አሁን ላይ ከአቅማቸው በታች እያመረቱ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማህበር አስታውቋል፡፡

በመሳይ ገ/ መድህን

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሕዳር 06 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.