መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ሌላ አዲስ ዙር ውይይት ይጀምራሉ የሚል ተስፋ አለን አለ ኢጋድ

ያለስምምነት በተጠናቀቀው የዳሬሰላሙ የሰላም ድርድርን ተከትሎ ኢጋድ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) ያልተፈቱ እና ቀሪ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በቀጠይ ሌላ ዙር የሰላም ድርድር ያዘጋጃሉ ብሎ እንደሚያምን አስታወቀ።

በማናቸውም መሰል የሰላም ድርድሮች ወቅት ውስብስ ነገሮች እና እንቅፋቶች ማጋጠማቸው የማይቀር መሆኑን ከቆየ ልምዱ ጋር በማጣመር ያነሳው ኢጋድ በመግለጫው ሁለቱም ተደራዳሪዎች ላሳዩት ቁርጠኝነት አድናቆቱን ገልጿል፤ ውይይቱ እንዲካሄድ አስተዋጽ አድርገዋል ያላቸውን አሜሪካ፣ ኖርዌይ እና ታንዛንያን አመስግኗል።

የኦሮምያ ክልልን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁለቱም አካላት ለሚያደርጉት ጥረት ኢጋድ ምንግዜም ድጋፉን ለመስጠት ዝግጁ ነው ሲል ገልጿል።

ኢጋድ በመንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል ያለው ችግር ተፈቶ ሰላም እንዲሰፍን አሁንም እንደሚሰራ የገለፀ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ሁኔታውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የማያቋርጥ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።

ኢጋድ በታንዛኒያው ድርድር መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በምን በምን ጉዳዮች እንዳልተስማሙ እንዲሁም አሉ ያላቸውን ቀሪ ችግሮች በይፋ አላብራራም።

በኦሮሚያ ያለው ግጭት እልባት እንዲያገኝ የሰላም ድርድር በማማቻቸትና በመምራት ረገድ ኢጋድ ከፍተኛውን ድርሻ እየተወጣ ነው።

ህዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.