በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው ውጊያ የማቆም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው ውጊያ የማቆም ስምምነት ጊዜያዊ ሲሆን ለአራት ቀናት እንደሚቆይም ተገልጿል።

በደቡብ እስራኤል የምትገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ የእስራኤል ጦር የተኩስ አቁም ፋታ እስከተጀመረበት የመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ጥቃቱ ቀጥሉ እንደነበር ገልጻለች፡፡

በሐማስ የተወሰዱ ከ200 በላይ ሰዎች መካከል 13 ህጻናት እና ሴቶች ዛሬ ከሰዓት 10 አካባቢ የሚለቀቁ ይሆናል ተብሉ ይጠበቃል፡፡በተከታዩቹ አራቱ ቀናትም 50 ታጋቾች ይለቀቃሉ ብሏል ቢቢሲ።

በልውውጡም እስራኤል በተለያዩ እስር ቤቶቿ ከሳረቻቸው በሺዎች ከሚቆጠሩ ውስጥ 150 ፍልስጤማውያን የሚለቀቁ ይሆናል።

ከሚለቀቁት ታጋቾች በተጨማሪ በየ10 ታጋቾች አንድ ቀን የውጊያ ፋታ ሊኖር እንደሚችልም ተጠቁሟል።

200 እርዳታ የጫኑ መኪናዎች፣ አራት ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እና እንዲሁም አራት የምግብ ማብሰያ የጫኑ መኪናዎች በግብጽ የድንበር ማቋረጫ በኩል ወደ ጋዛ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል። ግብጽ በየቀኑ 13 ሺህ ሊትር ናፍጣ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንደሚፈቀድም አስታውቃለች።

ይህ ማለት ግን ጦርነቱ አብቅቷል ማለት አይደለም ብሏል የእስራኤል መከላከያ ኃይል ፡፡

ለአራት ቀናት የሚቆየው የተኩስ አቁም ፋታ ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ የእስራኤል መከላከያ “ጦርነቱ አላበቃም ” ሲል በጋዛ ለሚኖሩ ፍልስጤማውያን አስጠንቅቋል።

“የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ፋታው ጊዜያዊ” ነው ሲሉም የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃለ አቀባይ አቪቻይ አድራይ በአረብኛ ቋንቋ ተናግረዋል።

“ሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ አደገኛ የጦር ቀጠና ነው እናም ወደ ሰሜናዊ ጋዛ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።

ለደህንነታቸው ስትሉ በደቡባዊ ጋዛ ባለው የሰብዓዊ ዞን ውስጥ መቆየት አለባችሁ” ሲሉ ለጋዛውያን ተናግረዋል።

እስራኤል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ያለችው ደቡባዊ ጋዛንም የማያባራ የአየር ጥቃት ስትፈጽምበት መቆየቱ ይታወሳል።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.