ኦዳ አዋርድ የምስራቅ አፍሪካ የጥበብ ሰዎችንም ሊሸልም ነው፡፡

7ተኛው የኦዳ አዋርድ ሽልማት የፊታችን ታህሳስ 11/2016 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡

በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ላይ ያሉ ባለሞያዎችን በማወዳደር የሚሸልመው “ኦዳ አዋርድ” በዚህ አመት ሰባተኛ ዙር የሽልማት መርሃ ግብሩን የፊታችን ታህሳስ 11 ያካሂዳል ተብሏል፡፡

ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎችም ቋንቋዎች በሃገራችን የተሰሩ የኪነጥበብ ስራዎችን ለማበረታታት በሚል የተጀመረው የሽልማት መርሃ-ግብሩ ታህሳስ 11/2016 በስካይ ላይት ሆቴል እንደሚካሄድ አዘጋጁ በሻቱ ቶለማሪያም መልትሚዲያ አስታውቋል።

ከባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ጋር በመተባበር የሚደረገው ይህ የሽልማት መርሃግብር የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትንም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚያሳትፍ ገልጿል።

በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 15 ሃገራት መካከል ኤርትራ፣ሱዳን እና ኬኒያን ጨምሮ 8 ሃገራት እንደሚሳተፉ ተነግሯል።

ባለፉት ስድስት አመታት በነበረው የሽልማት ስነስርዓትም ከ20 በላይ በሚሆኑ ዘርፎች 300 ለሚሆኑ ባለሞያዎች የእውቅና ሰርተፊኬትና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

ይህም ከፍተኛ መነቃቃትን በመፍጠር የኪነጥበብ ስራዎች በጥራት እንዲወጡ ማድረግ ችሏል ነው የተባለው።

የሰባተኛው ዙር ሽልማትም ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ፣በኪነጥበብ ምርምር ያካሄዱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የዳኝነት ሂደቱን እንደሚያካሂዱ ተገልጿል።

ታህሳስ 11 የሚደረገውም የሰባተኛው የኦዳ አዋርድ የሽልማት ስነ-ስርዓት በሙዚቃ ፣በመፅሐፍ እና በህይወት ዘመን ተሸላሚ በሚሉ ዘርፎች ተወዳዳሪዎችን ተሸላሚ ያደርጋል ተብሏል።

የ7ኛው ኦዳ አዋርድ የሽልማት ዘርፎች የህይወት ዘመን ተሸላሚን ጨምሮ

በሙዚቃ

  1. የአመቱ ምርጥ አልበም
  2. የአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ
  3. የአመቱ ምርጥ ቪዲዮ ክሊፕ
  4. የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ስቱዲዮ
  5. የአመቱ ምርጥ አዲስ ድምፃዊ
  6. የአመቱ ምርጥ ሴት ድምፃዊት
  7. የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ጥምረት
  8. የአመቱ ምርጥ ዘመናዊ ሙዚቃ
  9. የአመቱ ምርጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስት

በመፅሐፍ ዘርፍ

የአመቱ ምርጥ የልብወለድ መፅሃፍ
የአመቱ ምርጥ የግጥም መፅሃፍ የሚሉ ዘርፎችን የሚያካትት ይሆናል፡፡

ለዚህ አመት ለሽልማት የሚበቁ እጩ ስራዎች በ2015 ዓ.ም ከመስከረም 1 እስከ ጳጉሜ 6 የተሰሩ ብቻ እንደሚሆኑ የተገለፀ ሲሆን ዳኞች የራሳቸውን መስፈርት በጋራ በማውጣት እያንዳንዱን ስራ በጥልቀት በመመርመር ከ7ዐ ነጥብ የሚሰጡ ይሆናል፡፡

በዚህ መንገድ የተሻለ ነጥብ ያገኙት ስራዎች ለመጨረሻ የህዝብ ዳኝነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መላኪያ 8222 ላይ ድምፅ እንዲያገኙ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣይ አስራ አምስት ቀናት ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ተነግሯል።

በመሳይ ገ/መድህን

ህዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.