በ2017 ዓ.ም ዕድሜያቸዉ 9 ዓመት ለሞላቸዉ ሴት ልጆች የማህጸን በር ካንሰር ክትባትን በመደበኛነት መስጠት እንደሚጀምር ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በዚህኛዉ ዓመት ዕድሜያቸዉ ከ9-14 የሆኑ ከ8.8 ሚሊየን በላይ ሴት ልጆችን ለመከተብ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑንም ነዉ የገለጸዉ፡፡

ጤና ሚኒስቴር በ2011 ዓ.ም ዕድሜያቸዉ 14 ዓመት የሞላቸዉ ሴት ልጆችን የማህጸን በር ካንሰር ቅድመ መከላከል ክትባት መስጠት መጀመሩ የሚታወስ ነዉ፡፡

ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ እድሜያቸዉ 9 ዓመት ለሞላቸዉ ሴት ልጆች በመደበኛነት ክትባቱ እንደሚሰጥ በጤና ሚኒስቴር የክትባት አገልግሎት ዴስክ አማካሪ የሆኑት አቶ መንግስቱ ቦጋለ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ክትባቱ ከተጀመረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 ዓመታት በሁለት ዙር ክትባቱ ይሰጥ እንደነበር የገለጹት አቶ መንግስቱ ፤በዚህ ዓመት ግን በአንድ ዙር ብቻ ክትባቱ በዘመቻ መልክ እንደሚሰጥ ነግረዉናል፡፡

በዚህ 5 ዓመታት ጊዜ ዉስጥም የመጀመሪያ ዙር ክትባት የወሰዱ ሴቶች ቁጥር ከ6.3 ሚሊየን በላይ ሲሆን፤ ሁለተኛዉን ዙር የወሰዱ ሴት ልጆች ቁጥር ደግሞ 4.2 ሚሊየን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአገራችን በየዓመቱ ከ7ሺህ4መቶ በላይ ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር የሚያዙ ሲሆን፤ 5 ሺህ 3መቶ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸዉ ያልፋል ነዉ የተባለዉ፡፡

በአገራችን ከኮቪድ ጀምሮ ባለዉ 3 ዓመት ጊዜ ዉስጥ ከ20ሺህ በላይ ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ተይዘዉ ከ16ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸዉ ማለፉንም አማካሪዉ ነግረዉናል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ህዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.